ልማዳዊ የኢነርጂ አጠቃቀምን በዘመናዊ ዘዴ መተካት እንደሚገባ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ልማዳዊ የኢነርጂ አጠቃቀምን በዘመናዊ ዘዴ መተካት እንደሚገባ ተገለጸ

ሰኔ 25/2011 በአካባቢ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረውን ልማዳዊ የኢነርጂ አጠቃቀም በዘመናዊ ዘዴ መተካት እንደሚገባ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታወቀ። ለሁለት ቀናት የሚካሄደው የኢትዮጵያ ገጠር ኢነርጂ ልማት የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ዛሬ በሃዋሳ ከተማ ተጀምሯል። በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የማዕድንና ነዳጅ ሚንስትር ዲኤታ ዶክተር ኳንግ ቱትላም እንዳሉት ዘመናዊ ኢነርጂ ባልተዳረሰባቸው የሀገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች የአማራጭ ኢነርጂ መገልገያዎችና ቴክኖሎጂዎችን ለማስፋፋት በተቀናጀ መንገድ ጥናትና ልማት መካሄድ አለበት። በተለይ ለአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸውን የገጠር ኢነርጂ ቴክኖሎጂዎችን በማልማት ለህብረተሰቡ ማቅረብ እንደሚገባ ነው የገለጹት። ዶክተር ኳንግ እንዳሉት በገጠር ኢነርጂ ዘርፍ ኢትዮጵያ ከታዳሽ የኢነርጂ ምንጭ መጠቀም የሚያስችል ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብት ቢኖራትም ጥቅም ላይ ከማዋል አንጻር ክፍተቶች አሉ። በገጠሩ የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂና ሌሎች ማገዶ ቆጣቢ የሆኑ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ከመጠቀምና ከማስፋፋት አንጻር ያለውን ክፍተት መፈተሽ እንደሚገባም አመልክተዋል። የህብረተሰቡን የኢነርጂ አጠቃቀም ለማሻሻልና የማገዶ ፍጆታውን ለመቀነስ ዘመናዊ የኢነርጂ ምንጭ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ማቅረብ ግድ እንደሚልም ዶክተር ኳንግ ጠቁመዋል። ይህን ለማሳካት መንግስት የገጠር ኢነርጂ ልማት ማስፋፊያ ማዕከል እንዲቋቋም ማድረጉን ነው የጠቆሙት። እንደሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ ማዕከሉ በዋናነት የገጠሩን የኢነርጂ ፍላጎት፣ አቅርቦትና ፍጆታን በጥናት በመለየት በመረጃ ላይ የተመሰረተ የኢነርጂ አማራጭ ቴክኖሎጂዎችን ከሀገር ውስጥና ከውጪ በማቅረብ ላይ ይገኛል። በደቡብ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ የኢነርጂ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተከተል ማቲዮስ በበኩላቸው እንዳሉት በክልሉ በገጠርም ሆነ በከተማ ከሚኖረው ህዝብ 90 ከመቶ የሚሆነው ለማብሰያነት የሚጠቀመው የማገዶ እንጨት በመሆኑ በየዓመቱ በርካታ ሄክታር ደን እየወደመ ይገኛል። በክልሉ የተለያዩ አማራጭ የኢነርጂ ምንጮችን በመጠቀም ለማገዶ ተብሎ የሚወድመውን ደን ለመታደግ ልዩ ልዩ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል። "የፀሐይ እና የባዮጋዝ አማራጭ ቴክኖሎጂዎችን እንዲሁም ማገዶ ቆጣቢ ምድጃ በመጠቀም ሕብረተሰቡ የተፈጥሮ ሀብቱን እንዲንከባከብና የደን ውድመትን እንዲከላከል ለማድረግ የሚያስችሉ የሙከራ ሥራዎች በመሰራት ላይ ናቸው" ብለዋል። ለሁለት ቀናት በሚቆየው በእዚህ የምክክር መድረክ ላይ ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።