'ሮድና ቤልት' የሚሰኘውን የቻይና መንግስት የልማት መርሃ ግብር በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው - የገንዘብ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
'ሮድና ቤልት' የሚሰኘውን የቻይና መንግስት የልማት መርሃ ግብር በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው - የገንዘብ ሚኒስቴር
ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የቻይና መንግሥት የ'ሮድና ቤልት' የልማት ትብብር መርሃ ግብር በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የዝግጅት ሥራ እያከናወነች መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ። ባለፈው ሚያዚያ ወር በቻይና ርዕሰ መዲና ቤጂንግ በታካሄደው የሮድና ቤልት ልማት መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ዳግም የመርሃ ግብሩ አባል አገር ሆና ፈርማለች። ኢትዮጵያ በመጀመሪያው የመርሃ ግብሩ ምዕራፍ አምስት ዓመታት የተለያዩ ግዙፍ የመሰረተ-ልማት ግንባታ ሥራዎቿን ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው። ከአነዚህም መካከል 746 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የአዲስ አበባ-ጂቡቲ የባቡር መስመርና የአዲስ አበበ ቀላል ባቡር ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ ናቸው። ጎን ለጎን በኢትዮጵያ የቻይና ቀጥታ ኢንቨስትመንት ሥራዎች እንዲቀላጠፍም መርሃ ገብሩ ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረው መረጃዎች ያሳያሉ። በሁለተኛውም የመርሃ ግብሩ ምዕራፍም ኢትዮጵያ ይበልጥ ተጠቃሚ እንድትሆን የዝግጅት ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ገልጿል። ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ እንደተናገሩት በዚህኛው የመርሃ ግብሩ ምእራፍ ኢትዮጵያ የውጭ ንግድ ገበያ መዳረሻዋን ለመጨመር ትሰራለች። በተለይም ደግሞ የግብርና ሥራውን በማዘመንና እሴት በመጨመር የዓለም አቀፉ የእሴት ሰንለሰት አካልና ተጠቃሚ እንድትሆን ይደረጋል ብለዋል። ይህም ኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ ንግድ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋት በመግለጽ። በአብነትም በአሁኑ ወቅት የእንሰሳት ውጤቶች ማቀነባበሪያ በተለይም በስጋ ምርት ላይ የኢንደስትሪ ፓርክ መገንባቱን ጠቁመዋል። ያም ብቻ ሳይሆን በግብርና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችም ጭምር እሴቶችን ከፍ ለማድረግ ድጋፍ የተጀመሩባቸው ቦታዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል። በተጓዳኝም ቻይና የደረሰችበትን ከፍተኛ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ውጤቶች የመገልበጥና የመቅዳት ሥራዎችም እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ለአብነትም የቻይና የሳተላይት፣ የሚትዎሮሎጂ እንዲሁም የሪሞት ሴንስ ቴክኖሎጂዎች ትኩረት ተሰጥቷቸዋል ብለዋል። የታዳሽ ኃይል ልማት፣ የመንገድ መሰረተ-ልማት፣ የኢንደስትሪ ፓርክ ግንባታና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ሚኒስትር ዲኤታው ገልጸዋል። ከመርሃ ግብሩ የሚገኘው የገንዘብ ድጋፍም በረጅም ጊዜ የሚከፈልና የእዳ ጫና የማያመጣ ብድር (concessional loan) ብቻ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ አሁን በዓለም ባንክ የንግድና የኢንቨስትመንት ሥራ ለመሥራት ቀላል ናቸው ተብለው ከተጠቀሱት አገራት ዝርዝር፤ 159ኛ ደረጃ ይዛለች። በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጂያን የኢትዮጵያና የቻይና ግንኙነት ጠንካራ የደቡበ ለደቡብ ትስስር ማሳያ ነው ብለውታል። ቻይናና ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀው ይኸው ምጣኔ ኃብታዊ ግንኙነታቸው በዚህ የልማት ትብብር መርሃ ግብር ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2013 የተጀመረው የቻይናው የሮድ ኤንድ ቤልት የልማት መርሃ ግብር ለቀጣይ 30 ዓመታት ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል። እስካሁንም በመርሃ ግብሩ ማዕቀፍ ከአንድ ትሪሊዮን ዶላር በላይ ወጪ መደረጉን መረጃዎች ይጠቅሳሉ። እስካሁንም 124 አገራትና 29 ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በመርሃ ግብሩ በትብብር ለመሥራት ከቻይና መንግሥት ጋር ተፈራርመዋል። 'ሮድና ቤልት" የተሰኘው ይህ የቻይና መንግስት ዓለም አቀፍ የልማት መርሃ ግብር በተለይ በአፍሪካ መሰረተ ልማትን እና ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት የሚያስችል ዓይነተኛ የትብብር መስክ ተደርጎ እየተወሰደ መሆኑም ይነገራል።