ለወጣቱ የንባብ ባህል መጎልበት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
ለወጣቱ የንባብ ባህል መጎልበት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ
ሰኔ 25/2011 ወጣቱ የንባብ ባህሉ እንዲያድግና በምክንያት የሚያምን ዜጋ እንዲሆን በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተመለከተ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻህፍት ኤጀንሲ ከመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር “ክረምትን ከመጻህፍት ጋር!” በሚል መሪ ቃል ለአንድ ሳምንት የቆየ የንባብ ሳምንት በባሌ ሮቤ ከተማ አካሂዷል፡፡ በኤጀንሲው የሪከርድ ሥራ አመራር ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ታምራት በእዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የንባብ ባህሉ የዳበረና በምክንያት የሚያምን ወጣት ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ መስራት አስፈላጊ ነው። ወጣቱን ከአልባሌ ቦታዎች ለመከላከልና ከአደንዛዥ እጾችና አልኮል ሱሰኝነት ለማውጣት ኤጀንሲው በሀገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች የንባብ ሳምንት በማዘጋጀት በወጣቱ ዘንድ የንባብ ባህልን ለማሳደግ እየሰረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ እንደዳይሬክተሩ ገለጻ የንባብ ሳምንት በየጊዜው መዘጋጀቱ የወጣቶች የንባብ ባህል እንዲያድግ ከማድረጉ ባለፈ በአልባሌ ቦታዎች የመዋል ዝንባሌያቸው እንዲቀንስ ያደርጋል። በንባብ ሳምንቱ በከተማው በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ለሚገኙ የህግ ታራሚዎችና በመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ላሉ ተማሪዎች በንባብ ባህልና ሌሎች ተዘማጅ ጉዳዮች ላይ በኤጀንሲው ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ተሰጥቷል፡፡ ታዋቂ ደራሲያን የሕይወት ተሞክሯቸውን ለመርሃ ግብሩ ታዳሚዎችም አካፍለዋል። ኤጀንሲው ከ2 ሺህ በላይ መጻህፍት ለትምህርት ቤቶች፣ ለማረሚያ ቤቶች እንዲሁም ለህዝብ ቤተ መጻህፍት መለገሱንም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡ “የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የውጭና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ዶክተር ዘለቃ ረጋሳ በበኩላቸው የንባብ ሳምንቱ በየጊዜው እየቀነሰ የመጣውን የንባብ ባህል በማሰደግ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ለውጥ ውስጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ ወጣት ለማፍረት ይረዳል” ብሏል፡፡ ከንባብ ሳምንቱ ተሳታፊዎች መካከል የባሌ ሮቤ ማረሚያ ቤት የህግ ታራሚ ወጣት መንግስቱ ደረጀ በሰጠው አስተያየት ዝግጅቱ ለንባብ የነበረውን ዝቅተኛ ግምት እንዲለወጥ የረዳው መሆኑን ነው የገለጸው፡፡ በዝግጅቱ ላይ የንባብ ባህልን ማጎልበት ያለውን ፋይዳ ከመረዳቱ በተጨማሪ ከተዋቂ ደራሲያን የህይወት ተሞክሮ ብዙ ልምድ መቅሰሙን የተናገረው ደግሞ የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ኤብሳ አብዲሳ ነው፡፡