ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝን ለማሻሻል በትጋት እንደሚሰሩ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝን ለማሻሻል በትጋት እንደሚሰሩ ገለጹ
ሰኔ 25/2011 ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ቃለ-መሃላ የፈጸሙት አዲሱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ዶክተር ዴንኤል በቀለ ''በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝን ለማሻሻል በትጋት እሰራለሁ'' ብለዋል። ኮሚሽነሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ በኢትዮጵያ ቀደም ባሉት ዓመታት የሰብዓዊ መብት አያያዝ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደነበር ያስታውሳሉ። አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ይታዩ የነበሩ የከፉ ችግሮች ላይ የተወሰነ መሻሻሎች ቢኖሩም አሁንም ችግሩ ሙሉ ለሙሉ አለመወገዱን ገልጸዋል። ''ባለኝ የስራ ልምድና የትምህርት ደረጃ የአገሪቷ ሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ የድርሻዬን እንድወጣ ዕድሉን በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ'' ያሉት ኮሚሽነሩየተሰጣቸውን ሃላፊነት በብቃት ለመወጣት በትጋት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። ''ስራዬን ከማዳመጥ እጀምራለሁ'' ያሉት ዶክተር ዳንኤል በጉዳዩ ላይ ሚና ያላቸውን መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ግለሰቦችና ድርጅቶች በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ያላቸውን ሀሳብ እንደሚያዳምጡ ተናግረዋል። በአገሪቷ የመጣውን ለውጥ እንደ ዕድል በመጠቀም ለውጡ ወደሚፈለገው አቅጣጫ እንዲሄድና የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዲከበር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት የሚሰሩም አመልክተዋል። ዶክተር ዳንኤል በቀለ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በህግ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በአካባቢያዊና ማህበራዊ ልማት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል። በዓለም ዓቀፍ ህግና ሰብዓዊ መብት ህግ ጥናትም ሁለተኛ ዲግሪ በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ በማዕረግ ተመርቀዋል። ከዶክትሬት ዲግሪያቸውን በተመሳሳይ በኦክስፎረድ ዩኒቨርስቲ በዓለም ዓቀፍ ህግ አጠናቀዋል። በሰብዓዊ መብቶችና በጎ አድራጎት ድርጅቶች ልማት ተማራማሪና አማካሪ፣የአፍሪካ ሰብዓዊ መብት ዲቪዥን ዋና ዳይሬክተር፣ በግል የህግ ተቋም ጠበቃና የህግ አማካሪ እንዲሁም በተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች በአማካሪነት፣ ተመራማሪነትና በአሰልጣኝነት አገልግለዋል።