ቀጥታ፡

በሐረር ከተማ የተከሰተው እሳት በቁጥጥር ሥር ውሏል

ሐረር ሰኔ 25/2011 በሐረር ከተማ በተለምዶ ''መብራት ኃይል'' ተብሎ በሚጠራው ገበያ የተከሰተው እሳት በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ። የእሳት አደጋ ማጥፊያ ተሽከርካሪዎች ፈጥኖ አለመድረስ አደጋውን በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር አንዳላስቻላቸው ንብረት የወደመባቸው ነጋዴዎች ተናግረዋል። የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የክልሉ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ጣሰው ቻለው እንደገለጹት እሳቱን የክልሉና የፌዴራል ፖሊስና አንዲሁም የመከላከያ ሠራዊት አባላት ከኅብረተሰቡ ጋር ተቀናጅተው ባደረጉት ርብርብ ለመቆጣጠር ተችሏል። አደጋው ለሁለት ሰዓት ያህል ቆይቶ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ከ30 ላይ በቁጥጥር ሥር መዋሉንም አስረድተዋል። አደጋው ለጊዜው ግምቱ የማይታወቅ ንብረት መውደሙን የተናገሩት ኮማንደር ጣሰው፣የአደጋው መንስዔ በመጣራት ላይ መሆኑን አስረድተዋል። በገበያው በልብስ ስፌት ሥራ የሚተዳደሩትና አቶ ቢንሳ ብዙአየሁ በአደጋው ንብረት እንደወደመባቸው ተናግረዋል።በገበያው በተደጋጋሚ ጊዜ የሚከሰተውን እሳት ሥራቸውን ለማከናወን ችግር ፈጥሮብኛል ብለዋል። ''አደጋው ሲከሰትብኝ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። በዚህም ለበርካታ ንብረት ውድመት ተዳርጌያለሁ'' ያሉት በገበያው የተዘጋጁ አልባሳትን በመሸጥ የሚተዳደሩና በአደጋው ንብረታቸው የወደመባቸው አቶ መሐመድ አብደላ ናቸው። የእሳት አደጋ ማጥፊያ ተሽከርካሪዎች አደጋው ሲከሰት ፈጥነው አለመድረሳቸው ቃጠሎውን በፍጥነት በቁጥጥር ሥር ለማዋል አዳጋች እንዳደረገውም ገልጸዋል። በሐረር ከተማ በተለምዶ ''መብራት ኃይል'' በተባለው ገበያ በ2002ና በ2007 ተመሳሳይ የእሳት አደጋ መድረሳቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም