የኢህአዴግ ሥራ እስፈጻሚ ውሳኔ መንግስት ለዓለም አቀፍ ውሳኔዎች ተገዥነቱን ያሳየበትና ዲፕሎማሲዊ ብልጫ የወሰደበት ነው....ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የኢህአዴግ ሥራ እስፈጻሚ ውሳኔ መንግስት ለዓለም አቀፍ ውሳኔዎች ተገዥነቱን ያሳየበትና ዲፕሎማሲዊ ብልጫ የወሰደበት ነው....ምሁራን
ደሴ / ደብረ ብርሃን ሰኔ 2/2010 የኢትዮጵያ መንግስት የአልጀርስ ስምምነትን ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ መግለጹ ለዓለም አቀፍ ውሳኔዎች ተገዥነቱን ያሳየበትና ዲፕሎማሲዊ ብልጫ የወሰደበት ነው ሲሉ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ፡፡ በተመሳሳይ ከኤርትራ ጋር ለዓመታት የቆየውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መንግስት መወሰኑ ተገቢና ወቅታዊ መሆኑን ሁለት የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገልጸዋል። በወሎ ዩኒቨርሲቲ የስነ ዜጋና ስነ ምግባር መምህር አቶ ሰብስብ ሃዲስ እንዳሉት መንግስት የአልጀርሱን ስምምነት እንዳለ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ መስማማቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ "የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ውሳኔ ለዓመታት በአካባቢው ሰፍኖ የቆየውን ውጥረት በማርገብ በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል የነበረውን ወዳጅነት የሚያድስ፣ የአፍሪካ ቀንድን ሰላም የሚያጠናክር ነው" ያሉት ምሁሩ ውሳኔው የአገሪቱን ዲፕሎማሲያዊ አቅም ማደጉን ያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ "የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያ ያሳለፈችውን ውሳኔ አስመልክቶ ምንም ዓይነት ምላሽ እስካሁን ባይሰጥም የኢትዮጵያ መንግሥት የጀመረውን ዲፕሎማሲያዊ ብልጫ በማስቀጠል በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ውስጥ ያለውን ተቀባይነት ማጠናከር አለበት" ብለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ህግ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪና በወሎ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር የሆኑት አቶ ደጀን የማነ በበኩላቸው በአልጀርሱ ስምምነት መሰረት የድንበር ኮሚሽኑ የሚያሳልፈው ውሳኔ የመጨረሻና አስገዳጅ ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት የስምምነቱን ፓኬጅ ያለመርህ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ለመተግበር ያሳለፈው ውሳኔ ከህግ አንጻር ተገቢና ትክክለኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ "የኢትዮጵያ መንግስት ለዓለም አቀፉ ህግ ያለውን ተገዥነት በውሳኔው አረጋግጧል" ያሉት አቶ ደጀን ይህም አገሪቱ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ያላትን ተቀባይነት እንደሚያሳድገው ጠቅሰዋል፡፡ ሁለቱ አገራት የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ለመተግበር ወደ አፈጻጸም ከመግባታቸው በፊት ግልጽነት የጎደላቸው ውሳኔዎች ካሉ ጊዜ ሰጥቶ ማጥራት እንደሚገባም ምሁሩ አሳስበዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጥናት መምህር አቶ የሺዋስ ጥጋቡ በበኩላቸው በሁለት ወንድማማች ህዝቦች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን አለመተማመን በመቅረፍ በኩል ውሳኔው ዓይነተኛ ሚና እንዳለው አስታውቀዋል፡፡ የሥራ አስፈጻሚው ውሳኔ ለአገራቱና ለአፍሪካ ቀንድ አገሮች ከሚኖረው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አንጻር በመልካም ጎኑ ቢታይም በቀጣይ አተገባበሩ ላይ መንግስት ተገቢ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል። በተመሳሳይ በኢትዮጵያና በኤርትራ ለዓመታት የቆየውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መንግስት መወሰኑ ተገቢና ወቅታዊ መሆኑን ሁለት የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሙህራን ገልጸዋል። በዩኒቨርሲቲው የህግ መምህር አቶ ሆነልኝ ኃይሉ ለኢዜአ እንዳሉት ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነት ተቀብላ ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኗ በተለይ ባለፉት ሃያ ዓመታት በድንበር አካባቢ በውጥረትና በጭንቀት ለሚኖሩ የሁለቱ አገር ዜጎች እፎይታን የሚሰጥ ነው። "በአልጀርስ ስምምነት የተወሰነውን የአለም ዓቀፍን ህግ ተቀብሎ መተግበር ግዴታችን ነው" ያሉት አቶ ሁነልኝ፣ የስምምነቱ መተግበር ለሁለቱ አገራት ጥቅም ስላለው ወቅታዊና ትክክለኛ መሆኑን ተናግረዋል። "አገራቱ ወደሰላም መምጣታቸው ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለምስራቅ አፍሪካ አገራት ሰላምና የንግድ እንቅስቃሴ መጎልበት አስተዋጽኦ ይኖረዋል" የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የጀመረችውን የህዳሴ ጉዞ እውን ለማድረግም ሆነ ዕድገቷን በማስቀጠል ዜጎችን ተጠቃሚ ስለሚያደርግ መንግስት የጀመረውን የሰላም ጥሪ እጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል። "የተዋለድን፣ የተጋባን፣ በብዙ ነገር የተሳሰርንና የማንነጣጠል ህዝቦች በመሆናችን ጥላቻን በማስወገድ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማሀበራዊ ጉዳዮች ግንኙነትን ማጠናከር ይገባል" ብለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የስነ-ዜጋና ስነ-ምግባር መምህር አቶ ሀሳቡ ተስፋ በበኩላቸው ውሳኔው ሁለቱን አገራት ወደ ቀድሞው ግንኙነታቸው እንዲመለሱና ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ነው የገለጹት። "የዘገየ ውሳኔ ቢሆንም አሁን የተጀምረው የሰላም ጥሪም በአለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ተሰሚነት እንዲጎለብት የሚያደርግ በመሆኑ ትክክል ነው" ብለዋል፡፡ ሁለቱ አገራት በጥርጣሬ ከመተያየት ወጥተው ተግባብቶና ተስማምቶ ለአገርና ህዝብ የጋራ ተጠቃሚነት መስራታቸው ይበልጥ አዋጪ ስለሚሆን መንግስት ተገቢ ውሳኔ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራ የምስራቅ አፍሪካ እምብርት በመሆናቸው ለሌሎች አገሮች ስጋት ሳይሆን የሰላም ቀጠና መሆን እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል። የድንበር ጥያቄዎች በጦርነት ሳይሆን በድርድር መፈታት ስላለባቸው የተጀመረው የሰላም ጥሪ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።