በባሌ ዞን የኮሌራ በሽታ እንዳይከሰት የመከላከል ሥራ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በባሌ ዞን የኮሌራ በሽታ እንዳይከሰት የመከላከል ሥራ እየተሰራ ነው
ሰኔ 25/2011 በባሌ ዞን የክረምቱን ዝናብ ተከትሎ የኮሌራ በሽታ እንዳይከሰት ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ጤና ጽህፈት ቤት አስታወቀ። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የተለያየ ወረዳ የጤና ባለሙያዎችም የአካባቢ ንጽህና ጉድለት ችግርን ለማስወገድ ከማህበረሰቡ ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። የዞኑ ጤና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ እሸቱ ቶሎሳ ለኢዜአ እንደተናገሩት ጽህፈት ቤቱ በሽታውን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ተግባራትን እያከናወነ ይገኘል፡፡ ለእዚህም በየደረጃው ለሚገኙ የጤና ተቋማት ባለሙያዎች ስልጠና እየሰጠ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡ ምክትል ኃላፊው አቶ እሸቱ እንዳሉት ማህበረሰቡ የኮሌራ በሽታ መንስኤው የተበከለ ምግብና መጠጥ መሆኑን በመረዳት ለግልና ለአካባቢ ንጽህናው ትኩረት እንዲሰጥ በየደረጃው ያሉ የጤና ባለሙያዎች በማህበረሰብ ግንዛቤ ላይ አተኩረው በመስራት ላይ ናቸው። የበሽታውን ሁኔታ የሚከታተልና ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ግብረ ኃይል በዞኑ 18 ወረዳዎችና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች ውስጥ እንዲቋቋም መደረጉንም ገልጸዋል። ህብረተሰቡ ራሱን ከበሽታው ለመከላከል የኩሬና የምንጭ ውሃን በኬሚካል ከማከም ባለፈ ውሃ አፍልቶ እንዲጠጣና ምግቡን በንጽህና አብስሎ እንዲጠቀም አቶ እሸቱ አስገንዝበዋል፡፡ እስካሁንድረስ የበሽታው ወረርሽኝ በዞኑ አለመታያቱን ገልጸው፣ ህብረተሰቡ በሰዎች ላይ ተቅማጥና ትውከት ሲመለከት ወዲያውኑ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ጤና ተቋም በመሄድ እንዲታከም መክረዋል፡፡ ስልጠናውን ከተከታተሉ የጤና ባለሙያዎች መካከል የራይቱ ወረዳ ጤና ባለሙያዋ አበራሽ ደርቤ በስልጠናው ስለበሽታው ባህሪ፣ የመከላከያ ዘዴና ተዛማች ጉዳዮች ላይ በቂ ግንዛቤ ማግኘቷን ተናግረለች፡፡ በተለይ በሽታው በቀላሉ በንክኪና ንጽህናው በጎደለ ምግብና መጠጥ ስለሚተላለፍ ማህበረሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ከአካባቢው አባገዳዎችና የሃይማኖት አባቶች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ነው ያስረዳቸው። “በሽታው ቢከሰት ፈጥኖ ለመከላከል በቂ መድኃኒትና ለሕሙማን ሕክምና መስጫ ሥፍራ የማዘጋጀቱ ሥራ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል” ያሉት ደግሞ ከጊኒር ወረዳ የመጡት የጤና ባለሙያው አቶ ተስፋዬ ተክልዬ ናቸው፡፡ የጎባ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ በቀለች አለሙ በበኩላቸው እንዳሉት በአካባቢያቸው የተመደቡ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በተላላፊ በሽታዎችና በአካባቢ ንጽህና አጠባበቅ ላይ ተከታታይነት ያለው ትምህርት እየሰጧቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በጤና ባለሙያዎቹ ስለኮሌራ በሽታ መተላለፊያ ዘዴና ሊደረጉ በሚገቡ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ የቤት ለቤት ግንዛቤ በመሰጠት ላይ መሆኑንም አመልክተዋል። በባሌ ዞን ለማህበረሰቡ የጤና አገልግሎት የሚሰጡ ከ90 የሚበልጡ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ይገኛሉ።