ቀጥታ፡

የዩ ኤስ ኤይድ የ5 ዓመት የቲቢ መከላከል ፕሮጀክት ተጠናቀቀ

ሰኔ 22/2011 በአሜሪካው ዓለም አቀፍ የልማት ተራድዖ ድርጅት (ዩስ ኤድ) ቲብን ለመከላከል ባለፉት አምስት ዓመታት ሲካሄድ የቆየው ፕሮጀክት ተጠናቀቀ። ፕሮጀክቱ በ 42 ሚሊዮን ዶላር በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየ ሲሆን ከ490 ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረጉ ተጠቅሷል። ፕሮጀክቱ በቀዳሚነት አገሪቷ የቲቢ በሽታን ለመከላከል የምታደርገውን ብሔራዊ እንቅስቃሴ ለማጠናከር  ያለመ እንደነበርም ተገልጿል። የቲቢ በሽታን የመመርመርና የማከም አቅምን ለማጎልበትና በበሽታው የተጠቁ የማኅበረሰብ ክፍሎች ህክምና እንዲያገኙም ድጋፍ መደረጉ ተገልጿል። ለዚህም ደግሞ የሰው ኃይል ግንባታ ላይ በመሥራት፣ የፖለቲካ ቁርጠኝነትና የማኅበረሰቡ ተሳትፎ እንዲጎለብት ድጋፍ መደረጉም ተጠቁሟል። ይህም ደግሞ የቲቢ በሽታ ህሙማን መድሃኒታቸውን በጊዜ እንዲያገኙና ከበሽታው  እንዲያገግሙ አስተዋጽዖ ማድረጉም እንዲሁ። በዚህም በአገሪቷ በቲቢ በሽታ የሚደርሰውን የሞት ምጣኔ በእጅጉ ቀንሷል ነው  የሚለው የድርጅቱ ሪፖርት። ከአጠቃላዩ የቲቢ ህሙማንም፤ 75 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በሚወስዱት መድኃኒት በሽታውን ለመቋቋም አቅም እንደፈጠረላቸውም እንዲሁ። የዓለም ጤና ድርጅት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2018 በኢትዮጵያ 117 ሺህ 705 የቲቢ በሽታ ህሙማን መኖራቸውን አስታውቋል። ከእነዚህም መካከል 12 ሺ 810ሩ ህጻናት እንደሆኑ ታውቋል። በኢትዮጵያየዩ ኤስ ኤድ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ትሮይ ቤክማን ፕሮጀክቱ ባለፉት ዓምስት ዓመታት ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰዋል። ፕሮጀክቱ ከዚህ ቀደም በቲቢ ላይ የሚሰሩትን ሥራዎች ከግምት በማስገባትናየነበሩትን መልካም ተሞክሮዎች በማስፋት የተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል። በቀጣይም ፕሮጀክቱን አጠናክሮ ለመቀጠል እቅድ መኖሩን ገልጸዋል። የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ከበደ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ቲቢን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት አግዟል ብለዋል። በቀጣይም ከድርጅቱ ጋር በመሥራት የበሽታውን ስርጭት ለመግታት እንደሚሰራም ተናግረዋል። የቲቢ በሽታ በአሁኑ ወቀት በዓለም አቀፍ ደረጃ በገዳይ በሽታነት በዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም