ምክር ቤቱ በዘንድሮው የስራ ዘመን ምን አከናወነ? - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ በዘንድሮው የስራ ዘመን ምን አከናወነ?
አዲስ አበባ ሰኔ 24/2011ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአራተኛ ዓመት የስራ ዘመኑ ምን አከናወነ? ምክር ቤቱ የስራ ዘመኑን ለማጠናቀቅ ጥቂት ቀናቶች የቀሩት ሲሆን፤ በዛሬ ውሎው የ2011 በጀት ዓመት የመንግስት የስራ አፈጻጸም ሪፖርትን አድምጧል። አባላቱም በሪፖርቱ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎች አንስተው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ምላሽ አግኝተዋል። ኢዜአ በስፍራው በመገኘት "ምክር ቤቱ በዘንድሮው የስራ ዘመን ምን የተለያ ነገር አከናውኗል?" ሲል አባላቱን አነጋግሯል። አቶ አሸናፊ ጋእሚ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች ቁጥር ዝቅ እንዲል የተደረገበት በስራ ዘመኑ ከተሰሩ መሰረታዊ የአደረጃጀት ለውጦች ዋነኛው መሆኑን ይናገራሉ። በእነዚህ አደረጃጃቶች አማካኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ አስፈጻሚ አካላትን በነጥብ መመዘን ተችሏል ነው ያሉት። "በኢትዮጵያ የነፈሰው የነጻነት አየር ወደ ምክር ቤቱ በመግባት አባላቱ አስፈጻሚ አካላትን በነጻነት እንዲቆጣጠሩ አድርጓል" ሲሉ የተናገሩት ደግሞ አቶ መሃመድ አህመድ ናቸው። ምክር ቤቱ በዓመቱ የተለያዩ ህጎች ያሻሻለበት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል። ወይዘሮ ሀዋ አሊ በበኩላቸው የምክር ቤቱ አባላት "እኔ ለሀገሬ" በሚል መርህ ያለማንም ቀስቃሽ ወደተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋዋር ከማህበረሰቡ ጋር መወያየታቸውን ተናግረዋል። በዓመቱ በርካታ ህግና አዋጆች ለህዝብ በሚጠቅም ሚዛን ብቻ ተለክተው እንዲሻሻሉ ምክር ቤቱ በነጻነት ተሟግቷል ነው ያሉት። የተጀመረው አገራዊ ለውጥ በስራቸው ላይ ምቹ መደላድል መፍጠሩን በመጠቆም። ምክር ቤቱ በዘንድሮው የስራ ዘመኑ የሲቪልና ማህበረሰብ እንዲሁም የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ ማሻሻያ አዋጆችን ያጸደቀ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በአሉታዊ ጎኑ የምትነሳበትን የጸረ ሽብር፣ የሚዲያና ሌሎች መሰል አዋጆች ላይ ምክክር ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል። በተጨማሪ ምክር ቤቱ "አላስፈላጊ የስራ መደራረቦችን ለመቀነስ" በሚል ዓላማ የነበሩትን 20 የሚደርሱ የቋሚ ኮሚቴ አደረጃጃቶቹን ወደ 10 ዝቅ አድርጓል።