"የእግር ኳስ ሜዳ ኳስ እንጂ ፖለቲካ አይንከባለልበትም" ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ - ኢዜአ አማርኛ
"የእግር ኳስ ሜዳ ኳስ እንጂ ፖለቲካ አይንከባለልበትም" ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ
ሰኔ 24/2011 "የእግር ኳስ ሜዳ ኳስ በጥበብ ይንከባለልበታል እንጂ ፖለቲካ አይንከባለልበትም" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስምንተኛው ልዩ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የመንግስታቸውን የ2010 ዓ.ም በጀት ዓመት ሪፖርት አቅርበዋል። የምክር ቤቱ አባላት ሪፖርቱን ተከትሎ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን ስፖርታዊ ጨዋነትን አስመልክቶ የተነሳው አንዱ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሰጡት ምላሽ አሁን ባለው ሁኔታ ስፖርት እና ችግሩ ብለን እንዳናወራ መፍትሄ እንዳናስቀምጥ ስፖርቱ ራሱ እንደሌለና የሚከሰቱት ችግሮች በሌለ ነገር ላይ እየተፈጠሩ መሆኑን ገልጸዋል። "ስፖርት ባህሪው መንደር አይደለም የእግር ኳስ ሜዳ ኳስ በጥበብ ይንከባለልበታል እንጂ ፖለቲካ አይንከባለልበትም ኳስ በጥብብ በእውቀት የሚንከባለልበት ነው" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ፖለቲካው ከፓርላማ፣ከሆቴል እና ከሃይማኖት ተቋማት አልፎ ስታዲየም እንደገባና ህዝቡ የፖለቲካ ሀሳብ የሚገልጽበት የቦታ ምርጫ መለየት እንዳልቻለ ተናግረዋል። እግር ኳስ የሚያቀራርብ ድልድይ እርስ በእርስ የሚያስተዋውቅ መሆን እንዳለበትገልጸው መንግስት ለስታዲየሞች ግንባታ ከፍተኛ ሀብት እያፈሰሰ እንደሆነና ይሄንንም ከፖለቲካ አጽድተን መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል። አብዛኛው በእግር ኳሱ ያሉ ክለቦች በመንግስት በጀት እየተዳደሩ መልሰው በመንግስት ላይ ችግር እየፈጠሩ እንደሆነም ተናግረዋል። ስታዲየም ገብቶ ብሔርህ ማለት አስፈላጊ እንዳልሆነና ጊዜ ማባከን እንደሆነ ገልጸው በእግር ኳስ ሜዳዎች በሚታዩ ችግሮች ምክንያት የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር (ፊፋ) ኢትዮጵያ ላይ ቅጣት ሊጣልባት እንደሚችልም አመልክተዋል። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ስታዲየሞችን እስከ ማገድ የሚደርስ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችልም እንዲሁ። "ስፖርትን ከብሔር፣ ስፖርቱን ከፖለቲካ ካላወጣን ስፖርቱ አልነበረም ብቻ ሳይሆን ስፖርቱ አይፈጠርም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የስፖርት ተቋማት የስፖርቱን ስርአት እና መርህ መሰረት አድርገው መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በርካታ ስራዎች መስራት እንደሚጠበቀትም አመልክተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ገንዘብ እያፈሰሰን ሰው እንዲደባደብ መድረክ አናመቻችም'' ሲሉም ካልተስተካከለ መንግስት ሊወስድ ስለሚችለው እርምጃ ጠቁመዋል። እግር ኳሱ ተስፋ ኖሮት አፍሪካ እና ዓለም ላይ የሚያሳየን ነገር ቢኖር መልካም ነበር ይሆን ግን እየታየ አይደለም፤ ገንዘብ ከስረን ወጣትም መክሰር አንፈልግም'' በዚሁ ረገድ ያለውን ነገር ሚዛናዊ አድርጎ መሄድ ያስፈልጋል ብለዋል።