ማክሮ ኢኮኖሚው 9 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት ሊያሳይ ይችላል - ኢዜአ አማርኛ
ማክሮ ኢኮኖሚው 9 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት ሊያሳይ ይችላል
አዲስ አበባ ሰኔ 24/2011 በበጀት ዓመቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ዕድገት 9 ነጥብ 2 በመቶ ሆኖ ሊመዘገብ እንደሚችል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2011 በጀት ዓመት ሪፖረት ሲያቀርቡ ባለፉት አመታት አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ምጣኔ ተከታታይ እድገት ማሳየቱንና ለድህንት ቅነሳ በጎ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል። ይሁንና አገሪቷ ከምትከተለው የፋይናንስ ሞዴልና ባጋጣማት ወቅታዊ አገራዊ ቀውስ ምክንያት ከሶስት ዓመታት ወዲህ ቅናሽ ማሳየቱን ጠቅሰው፤ ከ2008 እስከ 2010 ዓ.ም አማካይ እድገት 8 ነጥብ 6 በመቶ ሆኖ መመዝገቡን ገልጸዋል። በ2010 በጀት ዓመት ደግሞ 7 ነጥብ 7 እድገት ማሳየቱን ገልጸው፤ በጀት ዓመቱም ስር የሰደደ የኢኮኖሚ ቀውስ እንዲያገግምና አገራዊ ኢኮኖሚ እንዲረጋጋ በሚያስችሉ የማሻሻያ ስራዎች ላይ ትኩረት መደረጉን በሪፖርታቸው ገልጸዋል። በ2011 በጀት ዓመት ከሸቀጦች ንግድ አፈጻጽም ዝቅተኝነት በስተቀር በአብዛኛው የማገገም ሁኔታዎች መታየቱንና በኢኮኖሚ ጠቋሚዎች መሰረትም በዘንድሮ ዓመት ኢኮኖሚው 9 ነጥብ 2 በመቶ የዕድገት ምጣኔ እንደሚኖረው አብራርተዋል። ኢኮኖሚውን ካጋጠመው ስር የሰደደ መዋቅራዊ ችግር በማላቀቅ እድገቱን ማስቀጠል የሚቻለው ለማክሮ ኢኮኖሚው የስራ እድል ፈጠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል። የአገሪቷ አጠቃላይ የስራ አጥ ቁጥር 11 ሚሊየን እንደሆነ በዓየመቱም ከ2 ሚሊየን በላይ ዜጋ ወደ ስር ፈላጊ ገበያ እንደሚወጣ ነው ያስረዱት። አሁን ላይ ግን ኢኮኖሚው የሚፈጥረው የስራ አድል ከ1 ሚሊየን እንደማይዘል ገልጸው፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በበጀት ዓመቱ ለጉዳዩ ትኩርት ተሰጥቶ የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን መቋቋሙን አንስተዋል። እስከ ቀጣዩ በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ ለ3 ሚሊየን ዜጎች በውጭና በአገር ውስጥ የስራ አድል ለመፍጠር መታቀዱን አብራርተዋል። በዘንድሮው በጀት ዓመት ለ1 ነጥብ 4 ሚሊየን ዜጎች በጥቃቅን አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት የስራ እድል መፈጠሩን አስታውሰው ካለው የስራ አጥ ቁጥር አንፃር በቂ አይደለም ነው ያሉት። በሌላ በኩል የገቢና ወጪ ንግድ አፈጻጸምን በተመለከተ በበጀት ዓመቱ ባለፉት 11 ወራት 178 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የተሰበሰበ ሲሆን ከቀሪ ጊዜያት ጋር ተጨምሮ ቢያንስ 189 ቢሊየን ብር ሊሰበሰብ ይችላል። ይህም ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 10 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ነው ያብራሩት። በበጀት ዓመቱ የውጭ ንግድን ለማሳደግ ጥረት ቢደረግም መሻሻል አለማሳየቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ያም ሆኖ ከአገልግሎት ዘርፍ የተገኘው የውጭ ንግድ 25 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንና በሸቀጥና በአገልግሎት ዘርፍ የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ገቢ 10 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ገልጸዋል። በሃዋላ፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና በሌሎች ዘርፎች በአጠቃላይ ባለፉት 11 ወራት 21 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልጸው፤ በቀጣይ የውጭ ንግድ አፈጻጽምን በማሻሻም የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል። በፋይናንስ ዘርፍ ረገድ ባለፉት 10 ወራት ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ሁሉም ባንኮች ያሰባሰቡት ተቀማጭ ገንዘብ 22 በመቶ፣ ያሰራጩት አዲስ ብድር 35 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንና ከዚህም ውስጥ የግል ዘርፍ ድርሻ 65 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል። የዋጋ ግሽበትን ከ10 በመቶ በታች ለማውረድ ጥረት ቢደረግም የዓመቱ አብዛኛው ወራት 12 በመቶ እንደነበር ገልጸው በግንቦት ወር ግን 16 ነጥብ 2 በመቶ ማሻቀቡን ነው የገለጹት። የዋጋ ግሽበት በኢንቨስትመንት ላይ ከሚያሳድረው ተዕጽኖ ባሻገር ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች የሚጎዳ ነው ብለዋል። ለዋጋ ግሽበት መንስኤ የሆኑ ችግሮችን ለይቶ እርምጃ ለመውሰድ ከፍተኛ የመንግስት ውሰኔ ሰጭ አመራሮችና ባለሙያዎች ያሉት ግብረ ሃይል ተቋቁሞ በግንቦት ወር ያሻቀበውን የግሽበት ሁኔታ በሰኔ ወር በተመሰነ መልኩ ለመቀነስ ሙከራ መደረጉን ነው ያብራሩት። በቀጣይም በተቀናጀ ጥረት የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል። ግዙፍ የመንግስት ፕሮጀክቶችን ወደ ግል የማዛወር ስራዎችን በተመለከተም የተፈለገውን ዓላማ እንዲያመጣ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው ብለዋል። ወደ ግል ለማዛወር በሚደረገው ቅደም ተከትልም በመጀመሪያ ዙር ኢትዮ ቴሌኮምና የስኳር ፕሮጀቶች፣ በሁለተኛ ዙር የሃይል ማማንጫዎች፣ የባቡርና የሎጀስቲክስ ፕሮጀቶች በመጨረሻም የኢትዮጵያ አየር መንገድና ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንደሚሆኑ ገልጸዋል።