ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የቦረናና የጉጂ ኦሮሞ አባ ገዳዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የቦረናና የጉጂ ኦሮሞ አባ ገዳዎች ገለጹ
ዲላ ሰኔ 2/2010 የቦረናና የጉጂ ኦሮሞ አባ ገዳዎች በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሚደርገውን ጥረት እንደሚያግዙ ገለጹ። የቦረና እና የጉጂ ኦሮሞ አባ ገዳዎች አገራዊ አንድነትን ለማረጋገጥ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝ ያላቸውን ዝግጁነት ተናግረዋል። የቦረና ኦሮሞ አባ ገዳ ሮቢ ጃርሶ እንደተናገሩት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ መንግስት እየወሰዳቸው ባሉ የመፍትሔ እርምጃዎች የህዝቡ ጥያቄዎች እየተመለሱ ነው፡፡ በተወሰኑ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ ከወራት በፊት የነበሩ የፀጥታ ችግሮች አሁን ቢረግቡም ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። "የቦረና ህዝብ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በሰላምና በፍቅር የመኖር የቆየ ባህል ያለው ነው" ያሉት አባ ገዳ ሮቢ ይህንን አጠናክሮ በማስቀጠል ባህላዊ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡ "ህዝቡ እኛን ይሰማናል በተለይ ወጣቱ ትውልድ ፊቱን ወደ ልማት ብቻ እንዲያዞር በማድረግና የአካባቢያችንን ሰላም በማረጋገጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ለአገራዊ ሰላምና አንድነት እያደረጉ ያሉትን ጥረት እናግዛለን" ብለዋል ፡፡ የጉጂ ኦሮሞ አባ ገዳ ሚደጋ ኔቴ በበኩላቸው የገዳ ሥርዓት የኦሮሞ ብቻ ሳይሆን መላው የኢትዮጵያ ህዝቦችን አቅፎ ማኖር የሚያስችል የሠላምና ዴሞክራሲ እሴቶች ያሉት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አባ ገዳ ሚደጋ እንዳሉት የጉጂ ህዝብ በገዳ ባህላዊ ሥርዓት ውስጥ የሚኖር በመሆኑ አባ ገዳዎችን የሚሰማና የሚያከብር ነው። ይህን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የአካባቢው ህዝብ ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጥና አገራዊ አንድነቱን በማጠናከር ከመንግስት ጎን እንዲቆም ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ገልጸዋል። ለ22 ዓመታት በጉጂ ዞን ነጌሌ ከተማ መኖራቸውን የሚናገሩት ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት የሆኑት አቶ መልዐከብርሀን ዝማርጌ በበኩላቸው ከተማዋ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ተፋቅረውና ተከባብረው በአንድነት የሚኖሩባት መሆኗን ገልፀዋል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ የሰላም እና የአንድነት እሴቶች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተሸረሸሩ በመምጣታቸው የህዝቡ አንድነት ሥጋት ላይ ወድቆ እንደነበር አስታውሰዋል ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በሰላማዊ የስልጠን ሽግግር ወደ አመራር ከመጡ በኋላ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች መኖራቸውን ገልፀው፣ በአሁኑ ወቅት የተገኘውን ሰላም አጠናክሮ ለማስቀጠል ልጆችን መምከርና ማስተማር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። ብሔርን መሰረት ያደረገ አገራዊ አንድነትን የሚሸረሽሩ ግጭቶች በየአካባቢው ተከስተው የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን የገለጹት ደግሞ በጉጂ ዞን የሊበን ወረዳ ነዋሪ አቶ ኮንሶሌ ጠቼ ናቸው፡፡ በአካባቢያቸው ያሉ ወጣቶች የአባቶቻቸውን ፈለግ ተከትለው ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በሰላምና በህብረት እንዲኖሩ አባታዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እንደሚሰሩም ገልፀዋል፡፡