የእንጀራ ፍላጎት በውጪ አገር እየጨመረ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
የእንጀራ ፍላጎት በውጪ አገር እየጨመረ መጥቷል
አዲስ አበባ ሰኔ 23/2011 የኢትዮጵያን ደረጃና የጥራት ቁጥጥር አልፎ ለአውሮፓ፣ አሜሪካና እስያ አገሮች የሚቀርበው የጤፍ እንጀራ ተፈላጊነቱ እየጨመረ በመምጣቱ የውጭ ምንዛሬ የማስገባት አቅሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዳደገ ተገለጸ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንጀራ " ከባዕድ ነገር ጋር ተቀላቅሏል" በሚል የሚሰራጨው መረጃ ደረጃውን ጠብቆ በሚዘጋጀውና ለውጭ ገበያ በሚቀርበው ምርት ላይ በደንበኞች ዘንድ ጥርጣሬ እንዲያድር ማድረጉ ተጠቁሟል። ከኢትዮጵያ የጤፍ እንጀራን በማዘጋጀት የአውሮፓና አሜሪካን አገሮችን ጨምሮ ወደ 16 የዓለም አገሮች የሚልከው "ዘዳግም ባልትና" ምክትል ስራ አስኪያጅ ወይዘሪት ብሩክታዊት አላምረው ከእንጀራ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ በየዓመቱ እየጨመረ መምጣቱን ይናገራሉ። እንደ ወይዘሪት ብሩክታዊት ገለጻ ፤ በባዕላት ወቅት በቀን እስከ 27 ሺ እንጀራ ተጋግሮ ወደ ውጭ በመላክ በዓመት እስከ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ያስገባሉ። እንጀራ ሲዘጋጅ ከእጅ ንክኪ ነጻ ሆኖ የቆይታ ጊዜውን በሚገልጽ መልኩ በማሸግና ደንበኞች በሚፈልጉት የደረጃና መጠን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ የሚገኘው ይሄው ተቋም አሁን አሁን ከእንጀራ ጋር ተያይዘው የሚሰራጩ ወሬዎች በደንበኞቻቸው ዘንድ ጥርጣሬን አስከትሏል። በአውሮፓ ፣ አሜሪካ እንዲሁም የእስያና አረብ አገሮች የእንጀራ ፈላጊዎች ቁጥርም እየጨመረ መምጣቱን የስታወሱት ወይዘሪት ብሩክታዊት ፤ በተለያዩ መንገዶች "እንጀራ ከባዕድ ነገር ጋር ይቀየጣል" በሚል የሚነዛው ወሬ የኢትዮጵያን ደረጃ በጠበቀ መንገድ ተጋግሮና የቁጥጥር መስፈርቶችን አልፎ ለውጪ ገበያ በሚቀርበው እንጀራም ላይ ደንበኞች እንዲጠራጠሩ እያደረገ መሆኑን ነው የገለጹት። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጤፍን ከተለየያ ባእድ ነገሮች ጋር በመቀላቀል እንጀራ ለአገር ውስጥ ገበያ የሚያቀርቡ ግለሰቦች መኖራቸው ጥራትና ደረጃውን ጠብቀው በሚያቀርቡት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ማሳደሩን ነው ያወሱት። "ዘዳግም ባልትና" ለ134 ሰራተኞች የስራ እድል ፈጥሮ እየሰራ ቢሆንም ዘርፉ ካለው አቅም አኳያ ግን ብዙ የስራ እድል የሚፈጥርና ብዙ ገቢ ሊገኝበት የሚያስችል መሆኑን ወይዘሪት ብሩክታዊት ያስረዳሉ። ከአስር በላይ አገራትን መዳረሻው ያደረገው "የሜሮብ እንጀራ" ስራ አስኪያጅ አቶ ሃብታሙ ጥላሁንም ድርጅታቸው በአመት ወደ 3 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ እንደሚያስገኝ ተናግረዋል። ወደ ውጭ የሚላከው የምርት መጠን በየዓመቱ ጭማሪ እያሳየ ቢመጣም አንዳንዶች በሚፈጥሩት ችግር በደንበኞች ዘንድ ጥርጣሬ እንዲኖር እያደረገ ነው ብለዋል። ከምርት ጥራት አቅርቦት ጀምሮ በጥንቃቄ የተዘጋጀ እንጀራ ወደ ተለያዩ አገሮች እንደሚልኩ የገለጹት አቶ ሃብታሙ ምርቱ የጥራት ማረጋገጫ ፍተሻዎችን አልፎ እንደሚላክም አረጋግጠዋል። የጥሬ ጤፍ ግብአትን በተመለከተ ከአምራቾች ጋር ቀጥታ ትስስር ፈጥረው እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ የኮሙንኬሽን ጉዳዮች ዳሬክተር አቶ ይስማ ጅሩ እንደሚሉት አስገዳጅ ካልሆኑ ከአስር ሺህ በላይ ደረጃዎች አንዱ የእንጀራ ምርት አቅርቦት ነው። ኤጀንሲው የአለም አቀፍ መስፈርትን መሰረት በማድረግና ከአዲስ አበባ ዩኑቨርስቲ ጋር በመተባበር ጥናት አድርጎ “የጤፍ እንጀራ” የተሰኘ ደረጃ አንዳዘጋጀ ገልጸዋል። የእንጀራ ደረጃ የሚለካውም በእንጀራው ይዘት፣ ስፋት፣ አይን፣ የአሲድ መጠን፣ የውሃ ይዘትና ሌሎችንም አሟልቶ በመገኘት ነው። ይህ አሰራርም ከሶስት አመት በፊት መውጣቱን አስታውሰዋል። ከሶስት አመት በፊት ደረጃው ወጥቶ እንጀራ ወደ ተለያዩ የአለም አገራት የሚልኩ ነጋዴዎችም አሰራሩን ተግባረዊ እያደረጉት እንደሚገኙ አብራትዋል። ወደ ተቀባይ አገራት የሚላከው እንጀራ ደረጃውን ማሟላቱን ተረጋግጦ መሆኑንም ጨምረዋል። የእስያና አረብ አገራትን ጨምሮ የጤፍ እንጀራ መዳረሻ አገራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመጠጥና የፋርማሲቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት መረጃ ያሳያል። የኢንሲትዩቱ ዋና ዳሬክተር አቶ ሰለሞን ታደለ እንደሚናገሩት ጤፍ ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ እየሆኑ ከመጡ ምርቶች አንዱ ነው። ከዘርገፉ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬም በ2007 ዓ.ም ከነበረው 3 ሚሊዮን ዶላር በ2010 ዓ.ም ወደ 15 ሚሊዮን ማደጉን ገልጸዋል። በ2011 በጀት አመት 9 ወራት ውስጥም ከ13 ሚሊዮን ዶላር በላይ ከዘርፉ ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል። ጤፍን ወደ እሴት ሰንሰለት ለመቀየር ኢንስቲትዩቱ በቴክኖሎጂ ድጋፍ፣ በእንጀራና በጤፍ ምርት ጥራት እንዲሁም በገበያ መዳረሻ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት። እንደ ዋና ዳሬክተሩ ገለጻ ለእንጀራ ምርት ጥራቱን የጠበቀ ጥሬ ጤፍ ለማቅረብ ላኪዎችን ከገበሬ ዩኒየኖች ጋር በማስተሳሰር ጥራቱን የጠበቀ ግብአት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው። የደረቅ እንጀራ ላኪዎች ያነሱትን ችግር ለመፍታት ከንግድና ኢንዱስትሪ ጋር በመተባበር ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እየሰሩ መሆኑን ነው የሚናገሩት። ዘርፉ የአገር ውስጥ ፍላጎትን በማይጎዳ መልኩ በርካታ የስራ እድል መፍጠር የሚያስችል ቢሆንም እስካሁን ብዙም አንዳልተሰራበት ያምናሉ። ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት ጤፍን ከደረቅ እንጀራ ባለፈ ዱቄትን ጨምሮ በተለያየ በልኩ በማቀነባበር ለመጠቀም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። የጤፍ እንጀራን ለውጭ ገበያ ከማቅረብ በተጨማሪ ዱቄቱንም ወደ ውጭ ለመላክ ጥናት መጠናቀቁን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ካላት አቅም ሃብት አንጻር ዘርፉ እንዳልተሰራበት የሚገልጹት ዋና ዳሬክተሩ በተለይም ከአገር ውስጥ አልፎ ወደ ተለያዩ አገራት በመላክ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት እንደ አማራጭ የታየው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው ብለዋል። በኢትዮጵያ ወደ ተለያዩ የአለም አገራት እንጀራ የሚልኩ 15 ላኪዎች ያሉ ሲሆን በ2010 ዓ.ም የእንጀራ ላኪዎች ማህበር መቋቋሙን ከኢንስቲትዩቱ የተገኘው መረጃ ያሳያል። ኢንስቲትዩቱ ወደ ዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው ባለሃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቋል።