ኤች አይ ቪ/ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት አመራሩ ማገዝ እንደሚገባው ጽህፈት ቤቱ አሳሰበ

ድሬዳዋ /ዓርባ ምንጭ ሰኔ 23 / 2011 ኤች አይ ቪ/ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት በየደረጃው የሚገኘው አመራር ማገዝ እንደሚገባው የፌደራል ኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አሳሰቡ፡፡ ጽህፈት ቤቱ በሽታውን አስመልክቶ በቀጣይ መስራት ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ከድሬዳዋ አስተዳደር አመራሮችና ባለድርሻዎች ጋር ተወያይቷል። የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፅጌረዳ ክፍሌ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት  ባለፈው ዓመት 13 ሺህ 300 ያህል ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ገልጸዋል። ከእነዚህም ውስጥ 3 ሺህ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት ናቸው ብለዋል። በአዋቂም ሆነ በወጣት እድሜ ክልል በሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ኤች አይ ቪ/ኤድስን የሚከላከሉበትና በዘርፉ ያለውን አገልግሎት የሚጠቀሙበት ግንዛቤና የባህሪ ለውጥ ዝቅተኛ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡ አመራሩ ለጉዳዩ በባለቤት በመሆን በሽታው በአገር እድገትና ህልውና ላይ የጋረጠውን ችግር መፍታት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሐር የኤች አይ ቪ ስርጭቱን ለመከላከል አመራሩ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል። በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ከፍተኛ አመራሮች ኤች አይቪ ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚከናወኑ ተግባራት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል፡፡ በውይይቱ የድሬዳዋ አስተዳደር አመራሮች ፣ የጤና ቢሮ ኃላፊዎች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ የእምነት ተቋማትና የማህበራት አመራሮች ተሳትፈዋል። በተመሳሳይ አምራች ዜጎችን እየቀጠፈ ያለውን ኤች አይ ቪ/ኤድስን ለመከላከል እየሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የዓርባ ምንጭ ዲስትሪክት ገልጿል። ”ተመርምረን እራሳችንን እንወቅ” በሚል መሪ ቃል ትናንት በተካሄደው የንቅናቄ መድረክ ከ200 በላይ የዲስትሪክቱ ሠራተኞች የኤች አይ ቪ ምርመራ አድርገዋል። የዲስትሪክቱ ኃላፊ አቶ አሰፋ አመለ እንደገለጹት ኤድስን የመከላከሉ ሥራ ከመደበኛ ሥራ እኩል ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው። ሠራተኞች በሥራቸው ባሀርይ መስክ ስለሚቆዩ ከቫይረሱ አጋላጭ መንገዶች ራሳቸውን እንዲጠብቁ የግንዛቤ ማስጨበጫ  ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። የዲስትሪክቱ ባልደረባ አቶ ዘርጉ ሰለሞን ለኤች አይ ቪ/ኤድስ የተሰጠው ትኩረት እየቀነሰ መምጣቱ ስርጭቱ ዳግም ማገርሸቱን አስረድተዋል። በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ ቢዳፌ በ11ዱም ሪጅኖች በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር 45 የዘርፉ ባለሙያዎች መመመደቡን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም