ዩኒቨርሲቲው በእንስሳት ሕክምናና አመጋገብ ትምህርት ክፍል ተማሪዎችን በሦስተኛ ዲግሪ ሊያሰለጥን ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው በእንስሳት ሕክምናና አመጋገብ ትምህርት ክፍል ተማሪዎችን በሦስተኛ ዲግሪ ሊያሰለጥን ነው
መቀሌ ሰኔ 2/2010 የእንስሳት ሕክምና ኮሌጅ በእንስሳት ሕክምናና አመጋገብ ትምህርት ክፍል በአራት የትምህርት ዓይነቶች ተማሪዎችን በሦስትኛ ዲግሪ ተቀብሎ ለማስተማር መዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡ ኮሌጁ በትምህርት ክፍሉ በአራት የትምህርት አይነቶች ተማሪዎችን በሦስትኛ ዲግሪ የትምህርት መርሀ ግብር ተቀብሎ ማስተማሩ በአገሪቱ የመጀመሪያ እንደሚያደርገው ተመልክቷል፡፡ ኮሌጁ ትምህርቶቹን ለማስጀመር ያዘጋጀውን ስርአተ ትምህርት አስመልክቶ ትናንት በኮሌጁ መሰብሰቢያ አዳራሽ የግምገማ መድረክ አካሂዷል፡፡ የኮሌጁ ዲን ዶክተር በሪሁ ገብረኪዳን በእዚህ ወቅት እንደገለጹት በአገሪቱ ያለው የእንስሳት ሃብት ከበሽታ ነፃ በማድረግ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ኮሎጁ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል፡፡ "የእንስሳት ሀብቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ በዘርፉ ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ማፍራት ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው" ብለዋል፡፡ በእዚህም በተመረጡ የእንስሳት ቀዶ ሕክምና፣ በእንስሳት አጠቃላይ በሽታዎች፣ በእንስሳት ምግብ ደህንነትና አመጋገብ፣ ከእንስሳት ወደ ሰው በሚተላለፉ በሽታዎች ላይ 20 ተማሪዎችን ተቀብሎ ከ2011ዓ.ም ጀምሮ በሦስተኛ ዲግሪ ማስተማር እንደሚጀምር አስታውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ያላት የእንስሳት ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዳይውል ከፍተኛ ማነቆ የሆነው የቴክኖሎጂና የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ኮሌጁ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራም ነው ዶክተር በሪሁ የገለጹት፡፡ ትምህርቱን ከሚቀጥለው መስከረም ወር ጀምሮ ለመስጠት ከኩባ፣ ከአሜሪካና በአገር ወስጥ ካሉ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የዘርፉ ምሁራን እንደሚመጡ አመልክተዋል፡፡ በዘርፉ በሦስትኛ ዲግሪ የሚማሩ ተማሪዎች በኮሌጁ የአራት ዓመት ቆይታ እንደሚኖራቸውም ዶክተር በሪሁ ተናግረዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተወክለው በአውደ ጥናቱ ላይ የተሳተፉት ዶክተር ኃይሉ ዳዲ በበኩላቸው እንዳሉት መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በሦስትኛ ዲግሪ የሚከፍታቸው የትምህርት አይነቶች በአገራችን እንስሳት ሀብት ላይ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ ነው፡፡ "በተለይም አገር በቀል የእንስሳት ዝርያዎችን የማሻሻል ሥራ ከተከናወነ የአለም ገበያ ላይ ለመወዳደር ያስችለናል" ብለዋል፡፡ ኮሌጁ ለመስጠት ያሰበውን የትምህርት አይነቶች በአገራችን በዘርፉ የሰለጠኑ የሰው ኃይል እጥረት ከመቅረፉ ባሻገር በእንስሳት ሀብቱ ላይ የሚታየውን በሽታና የአመጋገብ ስርአት ችግር የሚቀርፍ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ዶክተር ሸዊት ካልአዩ ናቸው፡፡ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በድህረ ምርቃና በሦስተኛ ዲግሪ የሚማሩ ተማሪዎች በጥናትና ምርምር ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ አበክሮ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ተቋሙ በ140 የሁለተኛ ዲግሪና በ16 የሦስተኛ ዲግሪ የትምህርት አይነቶች ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ እንሚገኝም ፕሮፌሰር ክንደያ አያይዘው ገልጸዋል፡፡