ቀጥታ፡

አክሱም ዩኒቨርሲቲ ኤርትራዊያን ተማሪዎችን አስመረቀ

ሰኔ 22/2011 የተጀመረው የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነትን ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ተመራቂ ኤርትራዊያን ተማሪዎች ተናገሩ። የጎንደር መምህራን ትምህርት ማሰልጠኛ ኮሌጅም በተለያዩ የትምህርት መስኮች ለሦስት ዓመት ያሰለጠናቸውን 1ሺህ 578 እጩ መምህራንን አስመርቋል፡፡ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ያስመረቃቸው 14 ኤርትራዊያን በመጀመሪ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ናቸው። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ኤርትራዊያን ተመራቂዎች እንዳሉት በቀጣይ የሁለቱን ሀገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ። በፓለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት የተመረቀው ዮናስ አሸብር እንዳለው የሁለቱ ሀገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ብዙ ዓመታት ያስቆጠረ ነው። ሀገራቱ በመካከላቸው ተፈጥሮ በነበረው አለመግባባት ከ20 ዓመታት መለያየት በኋላ ዳግም ግንኙነታቸውን ማደሳቸውን አስታውሶ  “በቀጣይ የሀገራቱን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ድልድይ ሆነን እንሰራለን “ብለዋል። ከዩኒቨርሲቲው በቢዝነስ ማኔጅመንት የተመረቀው ዮሐንስ ጉዕሽ በበኩሉ በኢትዮጰያ መንግስት የትምህርት ዕድል በማግኘቱ ደስታ እንደተሰማው ገልጾ "የጋራ ባህልና እሴት ያላቸው የኢትዮጰያና የኤርትራን ህዝቦችን  ማለያየት አይቻልም" ብሏል። በቀጣይም የሁሉቱ ሀገራት የጋራ ልማትና ተጠቃሚነት ለማሰቀጠል የበኩልን እንደሚወጣ ተናግሯል። “በሁሉቱ መንግስታት የተጀመረው ግንኙነት አስደስቶናል፤ የህዝቡም ፍላጎት ነው” ያለው ወጣቱ  የተጀመረውን የሀገራቱን ግንኙነት ማስቀጠል ደግሞ የእኛ ኃላፊነት ነው ብሏል። ተመራቂ ተማሪዎች፣ የተመራቂ ወላጆችና ቤተሰቦች የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል። በተያያዘ ዜና የጎንደር መምህራን ትምህርት ማሰልጠኛ ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ለሦስት ዓመት ያሰለጠናቸውን 1ሺህ 578 እጩ መምህራንን በዛሬው እለት በዲፕሎማ አስመርቋል፡፡ ከእውቀት ባለፈ በስነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ለመፍጠር ጠንክረው እንደሚሰሩ የኮሌጅ ተመራቂ እጩ መምህራን ተናግረዋል ከተመራቂ መምህራን መካከል በሒሳብ ትምህርት ክፍል የተመረቀችው መምህርት ስንቂት ማሙየ እንዳለችው በቀጣይ እውቀቷን ለተማሪዎች ከማካፈል በተጨማሪ ሀገራቸውን የሚወዱና በስነ ምግባራቸው የተመሰገኑ ተማሪዎችን ለማፍራት በኃላፊነት እንደምተሰራ ተናግራለች። ‹‹ሀገራችን ከመምህራን ብዙ ትጠብቃለች፤ እኛ መምህራንም ትውልድን በእውቀት አንፀን በመቅረፅ ለሀገራቸው እድገት ከፍተኛ ሚና እንዲጫወቱ ማድረግ አለብን” ብላለች። በማህበራዊ ሳይንስ እጩ መምህርና በኮሌጁ 3 ነጥብ 8 በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ የሆነው መንግስቱ ማሬ በበኩሉ ቀጣዩ ትውልድ በእውቀት የዳበረና ማህበረሰቡን አገልጋይ እንዲሆን በተመደበበት የስራ ቦታ ተማሪዎቹን እንደሚያበቃ ተናግሯል፡፡ ‹‹መመረቅ የመጨረሻ ሳይሆን ለአስተማረችኝ ሀገሬና ወገኔ አገልግሎት መስጠት የምጀመርበት ነው “ ያለው ተመራቂው ሲሆን በቀጣይም እውቀቱን በማዳበር የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ የመቅረፅ ኃላፊነቱን በብቃት ለመወጣት መዘጋጀቱን አስረድቷል፡፡ ‹‹የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች እውቀትንና ማህበራዊ ግብረ ገብነትን ይዘው እንዲያድጉ ማድረግ በቀጣይ የስራ ዘመኔ የምከተለው መርህ ነው፤›› ያለችው ደግሞ በስነዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት ዘርፍ የተመረቀችው መምህርት መሰረት የኔሁን ናት፡፡ የኮሌጁ ዲን አቶ ስንታየሁ ነጋሽ በበኩላቸው ኮሌጁ ከተቋቋመ 38 ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑን ጠቅሰው በእነዚህ ዓመታት ከ44 ሺህ በላይ መምህራንን ማስመረቁን ተናግረዋል። በዛሬው እለት ከተመረቁ 1ሺህ 578 እጩ መምህራን መካከልም 798ቹ ሴቶች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ እንደ ዲኑ ገለጻ ተመራቂዎቹ በትምህርት ቆይታቸው በቂ እውቀት ይዘው መውጣት የሚያስችላቸውን የተግባርና የንድፈ ሀሳብ ትምህርት አግኝተዋል። ምሩቃን በቀጣይ ሙያውን አክብረው በመስራትና ራሳቸውን ወቅቱ በሚፈልገው ልክ አቅማቸውን በማሳደግ ለትምህርት ጥራት መሻሻል ሀላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም