በፕሪሚየር ሊጉ መሪው ፋሲል ከነማ ነጥብ ሲጥል መቐለ 70 እንደርታ አሸነፈ

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መሪው ፋሲል ከነማ ነጥብ ሲጥል ተከታዩ መቐለ 70 እንደርታ በማሸነፍ ከመሪው ጋር ያለውን የነጥብ  እኩል አድርጓል። በአዲስ አበባና በባህርዳር በነበረው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ያልተካሄዱ የ28ኛ ሳምንት ቀሪ ጨዋታዎች ዛሬ ተካሄደዋል። በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማ ከፋሲል ከነማ ያደረጉት ጨዋታ 1 ለ 1 በሆነ የአቻ ውጤት  ተጠናቋል። ፋሲል ከነማ ከእረፍት በፊት ሙጂብ ቃሲም በፍጹም ቅጣት ምት ባስቆጠራት ግብ መሪ ቢሆንም ከእረፍት መልስ ቡልቻ ሱራ በግንባሩ በመግጨት ያስቆጠራት ግብ አዳማ ከተማን አቻ አድርጋለች። ውጤቱን ተከትሎ ፋሲል ከነማ ነጥቡን ወደ 53 ከፍ በማድረግ በሊጉ መሪነት ሲቀጥል አዳማ ከተማ ነጥቡን ወደ 35 በማሳደግ ከነበረበት 12 ደረጃ ወደ 10ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችሏል። በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ መቐለ 70 እንደርታ ደቡብ ፖሊስን 4 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት በማሸነፍ ነጥቡን ከፋሲል ከነማ ጋር እኩል አድርጓል። ለመቐለ 70 እንደርታ ጋናዊው አጥቂ ኦሴይ ማውሊ ሁለት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ፣ አማኑኤል ገብረሚካኤልና ያሬድ ብርሃኑ አንድ አንድ ግብ አስቆጥረዋል። በሃዋሳ ስታዲየም ሲዳማ ቡና በሀብታሙ ገዛኸኝ ብቸኛ ግብ ድሬዳዋ ከተማን 1 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል። በአዲስ አበባና በባህርዳር በነበረው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ተራዝሞ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 11 ሰአት ቅዱስ ጊዮርጊስና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሊያደርጉት የነበረው የ28ኛ ሳምንት ጨዋታ በጸጥታ ስጋት ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ መራዘሙን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። የሁለት ሳምንት መርሃ ግብሮች በቀሩበት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫውን ለማንሳትና ላለመውረድ እየተካሄደ ያለው ፉክክር ከሳምንት ሳምንት ይበልጥ አጓጊ እየሆነ መጥቷል። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ፋሲል ከነማና መቐለ ሰብዓ እንደርታ በተመሳሳይ 53 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን የያዙ ሲሆን ሲዳማ ቡና በ52 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። መከላከያ፣ ደቡብ ፖሊስና ቀድሞ ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዱን ያረጋገጠው ደደቢት ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ። የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ግብ አግቢነት የመቐለ ሰብዓ እንደርታው አማኑኤል ገብረሚካኤል በ16 ግቦች ሲመራ፤ የፋሲል ከነማው ሙጂብ ቃሲምና የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በተመሳሳይ 15 ግቦች ይከተላሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም