ቀጥታ፡

ወልቂጤ ከተማ በኢትዮጵያ ሴቶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ሆነ

አዲስ አበባሰኔ 2/2010 ወልቂጤ ከተማ የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን ሆኗል። ዛሬ ወልቂጤ ላይ ከቀኑ 7 ሰአት በተካሄደው የፕሪሚየር ሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ ጎንደር ከተማን 53 ለ 41 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የዘንድሮ የሊጉ አሸናፊ መሆኑን አረጋግጧል። ሁለቱ ቡድኖች ጨዋታቸውን ከማድረጋቸው በፊት ተመሳሳይ ዘጠኝ ነጥብ ነበራቸው። ወልቂጤ ከተማ ማሸነፉን ተከትሎ በ11 ነጥብ መሪ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ጎንደር ከተማ 10 ነጥብ በመያዝ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሶስተኛ አማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን አራተኛ ደረጃን በመያዝ ሊጉን አጠናቀዋል። ወልቂጤ ከተማ የሊጉ ሻምፒዮን መሆኑን ተከትሎ የዋንጫ ሽልማትና የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘ ሲሆን ጎንደር ከተማና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል። የወልቂጤ ከተማ አሰልጣኝ ዘመዴ በቀለ የ2010 ዓ.ም ኢትዮጵያ ሴቶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ አሰልጣኝ በመባል የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። የጎንደር ከተማዋ ህይወት ሺመልስ የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ተጫዋች በመባል የሜዳሊያ ሽልማት አግኝታለች። የአማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን ተጫዋቿ ሰናይት ታዬ በሊጉ 10 ጊዜ ሶስት ነጥብ የሚያስገኝ ቅርጫት በማስቆጠር የዓመቱ ምርጥ የሶስት ነጥብ አስቆጣሪ በሚል የሜዳሊያ ሽልማት አግኝታለች። የፌዴራል መንግስት ቤቶች ኮርፖሬሽን የባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ሴቶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል። በተያያዘ በወንዶች የሚካሄደው የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የ13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በራስ ሃይሉ ጅምናዚየምና ወልቂጤ ላይ ተካሂደዋል። በዚሁ መሰረት በራስ ሃይሉ ጅምናዚየም በተደረገው ጨዋታ ሃዋሳ ከተማ ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርትን 65 ለ 53 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። ወልቂጤ ላይ የሊጉ መሪ ወልቂጤ ከተማ ጎንደር ከተማን 62 ለ 48 በሆነ ውጤት ረቷል። በራስ ሃይሉ ጅምናዚየም የካ ክፍለ ከተማ ከአዳማ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በ37ኛው ደቂቃ አዳማ ከተማ 50 ለ 31 እየመራ ተቋርጧል። የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ከፍተኛ የውድድር ባለሙያ አቶ አብዱልፈታ ተማም ጨዋታው የተቋረጠበት ምክንያት እንዳልታወቀ ገልጸው ምክንያቱ የሚረጋገጠው የጨዋታው ኮሚሽነር ለውድድርና ስነ ስርአት ኮሚቴ በሚያቀርቡት ሪፖርት እንደሆነ ተናግረዋል። ኮሚቴው የሚቀርበውን ሪፖርት በመገምገም ከነገ በስቲያ በተቋረጠው ጨዋታ ላይ ውሳኔውን እንደሚያሳልፍ ጠቁመዋል። ዛሬ በራስ ሃይሉ ጅምናዚየም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ድሬዳዋ ከተማ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ የትራንስፖርት አቅርቦት ችግር ስላጋጠመው ጨዋታው ነገ ከረፋዱ 4 ሰአት ላይ በራስ ሃይሉ ጅምናዚየም እንዲካሄድ ፌዴሬሽኑ ወስኗል። ሰኔ 10 ቀን 2010 ዓ.ም በሚካሄዱት የመጨረሻ ሳምንት መርሃ ግብሮች የሊጉ አሸናፊ የሚለይ ይሆናል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም