በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ እየተፈጠሩ ባሉ ችግሮች ዙሪያ ለመምከር አስቸኳይ ስብሰባ ተጠራ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ እየተፈጠሩ ባሉ ችግሮች ዙሪያ ለመምከር አስቸኳይ ስብሰባ ተጠራ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 24/2010 በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እየታዩ ባሉ ችግሮች ዙሪያ የሚመክር አስቸኳይ ስብሰባ ነገ ይካሄዳል። በደጋፊዎች የሚፈጠር ረብሻና በአንዳንድ ጨዋታዎች ዳኞች ላይ እየተፈጸመ ያለው ድብድባ የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድርን የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት በስፋት እንዲታይ ከማድረጉ ባለፈ በተወዳጁ ስፖርት ላይ ጥላ እንዲያጠላበት አድርጓል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ዳንኤል ዘርአብሩክ ለኢዜአ እንደገለጹት በእግር ኳስ ሜዳዎች እየተባበሰ ለመጣው የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት መፍትሔ ለመስጠት ስብሰባው ተጠርቷል። በስብሰባው ላይ በፕሪሚየር ሊጉ የሚሳተፉ የ16 ክለቦች ስራ አስኪያጆች፣የፌደሬሽኑ አመራሮችና የይግባኝ ሰሚ፣የሊግ፣የስነ ምግባርና ሌሎች ኮሚቴዎች ሰብሳሳቢዎች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል። በአሁኑ ሰአት እየተፈጠረ ያለውን ችግር መፍታት የሚያስችሉ የመፍትሔ ሀሳቦች በማስቀመጥና የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ አቅጣጫ ማስቀመጥ የውይይቱ ዋነኛ አላማ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ፌደሬሽኑ አሁን እየተከሰቱ ባሉ ችግሮች ምክንያት የፊታችን ቅዳሜና እሁድ ሊካሄዱ የነበሩ የ23ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ሌላ ጊዜ እንዲካሄዱ መወሰኑን ተናግረዋል። በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ላልተወሰነ ጊዜ ተቋርጧል በሚል እያቀረቡት ያለው መረጃ ሀሰትና ከእውነት የራቀ መሆኑን አቶ ዳንኤል አስረድተዋል።