ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ኬንያ ግንኙነታቸውን የጀመሩበትን 55ኛ ዓመት አከበሩ

አዲስ አበባ ሰኔ 22/2011  ኢትዮጵያና ኬንያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩበትን 55ኛ ዓመት ሰሞኑን የአገሮቹ ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች፣ ተቀማጭነታቸውን በናይሮቢ ያደረጉ የዲፕሎማሲ ማህበረሰብ አባላትና በኬንያ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት ተከብሯል። በዓሉ ሲከበር ከናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡበት መድረክ የተዘጋጀ ሲሆን የሁለቱን አገሮች ግንኙነት በሚያሳዩ የፎቶና የስዕል አውደ ርዕይም ቀርቧል። በኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአስተዳደር ዘርፍ ምክትል ሚኒስትር አምባሳደር አባቡ ናምዋምባ ሁለቱ አገሮች የጠበቀና ዘርፈ ብዙ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰዋል። በሁለቱ አገሮች መንግስታትና ሕዝቦች መካከል ያለው ጠንካራ ወዳጅነት በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በመሰረተ ልማት ትስስር፣ በቀጣናዊ ሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች የላቀ ውጤት በሚያመጣበት ሁኔታ ላይ መጠናከር እንደሚገባው ገልጸዋል። በኬንያ ውስጥ የሚኖሩና በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ኢትዮጵያውያንም መብታቸው ተከብሮና ተጠብቆ እንዲኖሩ መንግስት እንደሚሰራ አስታውቀዋል። በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም በኩላቸው ''ኢትዮጵያና ኬንያ በመተባበር መንፈስና በጥሩ ጉርብትና ላይ የተመሰረት ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረ ተምሳሌታዊ ግንኙነት አላቸው'' ብለዋል። አምባሳደር መለስ “ኢትዮጵያና ኬንያ፡ የ55 ዓመታት ስትራቴጂካዊ አጋርነት” በሚል መሪ ሐሳብ በዓሉ መከበሩን አንስተው ሁለቱ አገሮች ይህንን ታሪካዊ ቀን ሲያከብሩ ሰላምን፣ መረጋጋትን እንዲሁም ወንድማማችነትን በመዘከር እንደሆነም አመልክተዋል። በሁለቱ አገሮች ሕዝቦችና መንግስት መካከል ያለው እድሜ ጠገብና ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከኬንያ የቅኝ ግዛት ነጻ መውጣት የሚቀድም መሆኑን የገለጹት አምባሳደር መለስ በመንግስት ለውጥ የማይዋዥቅ፣ ከመፎካከር ይልቅ በመተባበር ላይ ያተኮረ መሆኑን ተናግረዋል። ወደፊት ግንኙነቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በተለይም በመሰረተ ልማት፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በሌሎች ወሳኝ የትብብር ዘርፎች ለማስተሳሰር ከኬንያ የመንግስት መዋቅሮችና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ጋር ኢትዮጵያ ትኩረት ሰጥታ እንደምትሰራ ጠቁመዋል። ኢትዮጵያና ኬንያ ይፋዊ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን ቀን በ1964 ሲሆን ያለምንም ቪዛ የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች ነጻ እንቅስቃሴ በማድረግ ከአፍሪካ በግንባር ቀደምነት እንደሚጠቀሱ ኤምባሲው በላከው መግለጫ አመላክቷል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም