የሀጂና ኡምራ ጉዞ የተፈቀደዉ ለመንፈሳዊ ተጓዦች ብቻ ነዉ - ኢዜአ አማርኛ
የሀጂና ኡምራ ጉዞ የተፈቀደዉ ለመንፈሳዊ ተጓዦች ብቻ ነዉ
ሰኔ 22/2011 የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሀጂና ኡምራ ጉዞ የተፈቀደዉ ለመንፈሳዊ ተጓዦች ብቻ ነዉ አለ። ከዚህ ዉጪ የሚጓዙ ተጓዦች ሌሎች አማራጮችን ሊጠቀሙ እንደሚገባም ምክር ቤቱ ጠቁሟል። ምክር ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አንዳንድ ሰዎች በሀጂ ጉዞ ምክንያት ለስራና ለተለያዩ አላማዎች እንደሚሄዱና ይህ ሊቆም እንደሚገባ አሳስቧል፡፡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሃጂ እና ኡምራ ዘርፍ ሃላፊ ሼህ ኑረዲን ደሊል፤ ህዝበ ሙስሊሙ የሃጅ ስርአትን ለማከናወን ብቻ ሊሄድ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል። እስካሁን ከአስራ ሁለት ሺ በላይ ሰዎች መመዝገባቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ስምንት ሺ ሰዎች የሀጂ እውቅና ቁጥር ተሰጥቷቸው ለጉዞው ዝግጁ እንደሆኑ ተጠቅሷል። የሳኡዲ መንግስት ለስምንት ሺ ኢትዮጵያውያን ኮታ የሰጠ ቢሆንም የተጓዦች ፍላጎት በመጨመሩ ከ12 ሺ እስከ 15 ሺ ሰዎች እድሉን እንዲያገኙ ምክር ቤቱ ከሳውዲ መንግስት ፈቃድ በመጠበቅ ላይ መሆኑን ሼህ ኑረዲን አስታውቀዋል ፡፡ የሃጅ እና ኡምራ ጉዞ ክፍያ ከ 98 ሺ ወደ 78 ሺ አንድ መቶ ሀምሳ ብር ዝቅ መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡ ለ1 ሺህ 440ኛ ጊዜ የሚደረገው የሀጂና ኡምራ ጉዞ ከሀምሌ 3 ጀምሮ እንደሚጀመር በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡