ቀጥታ፡

የኦቶና ሆስፒታል የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ተገልጋዮችን እያማረረ ነው

ሰኔ 22/2011 በወላይታ ሶዶ በሚገኘው ኦቶና ሆስፒታል እየተስተዋለ ባለው የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለእንግልት እየተዳረግን ነው ሲሉ ተገልጋዮች ብሶታቸውን ተናገሩ፡፡ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያና ሪፌራል ሆስፒታል በበኩሉ ችግሩን ለማቃለል የሚያስችል የግብአትና የሰው ኃይል የማደራጀት ሥራ በመጀመሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሩ እንደሚፈታ አመልክቷል፡፡ ከጎፋ ዞን ለተመላላሽ ህክምና እንደመጡ የተናገሩት አቶ ሃይማኖት ዘውዴ በሰጡት አስተያየት ባለሙያዎች ሰዓታቸውን አክብረው እንደማይገቡና ሕሙማን ታክመው ሳይጨርሱ ቀድመው ጥለው ስለሚወጡ በሆስፒታሉ ተጨማሪ ቀናትን በማሳለፍ ለእንግልት መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ የጥበቃና የካርድ ክፍል ሰራተኞች ጭምር በትህትና እንደማያስተናግዱ ገልጸው በአካባቢው ሌላ ሪፌራል ሆስፒታል አለመኖሩ ችግሩን እያባባሰው መሆኑን ገልጸዋል ። የአዕምሮ ህመምተኛ ለሆነው ልጃቸው በየወሩ የሚሰጠውን ህክምና ለመከታተል መጥተው ተረኛ ኃኪም ጋር ሲደርሱ ካርዱ መጥፋቱን እንደተነገራቸው የገለፁት ደግሞ ከዳሞት ሶሬ ወረዳ የመጡት አቶ ስምኦን ግዳቦ ናቸው፡፡ ካርዱ ባለመገኘቱ ምክንያት ያለምንም ህክምና ለሁለት ቀናት መቆየታቸውንና በገንዘብ እጦት በሆስፒታሉ ጊቢ ውስጥ ለማደር መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡ የልጃቸው ሕመም በፍጥነት መድኃኒትና ሕክምና የሚፈልግ በመሆኑ የሚመለከተው አካል ችግሩን ፈትቶ እንግልታቸውን እንዲቀንስላቸውም ጠይቀዋል፡፡ በሆስፒታሉ የተመላላሽ ሕክምና ክፍል ኃላፊ አቶ እንዳለ ይገዙ በበኩላቸው ከካርድና መሰል የታካሚዎች የመረጃ አያያዝ ጋር በተፈጠረው ክፍተት ከተገልጋዮች እየተነሳ ያለውን ቅሬታ  ትክክል  መሆኑን አምነዋል፡፡ በሆስፒታሉ ያለው የካርድና ተያያዥ የመረጃ አያያዝ ያለመዘመኑ የችግሩ ዋንኛ ምክንያት መሆኑን አንስተው ተገልጋዮችም ለማመሳከር የሚሆኑ በቂ መረጃዎችን ይዘው አለመቅረባቸው ችግሩን እያባባሰው መሆኑን ተናግረዋል ። የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ሉቃስ ዲንጋቶ በበኩላቸው ተገልጋዩ ህብረተሰብ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች መሰረት በማድረግ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ "አገልግሎቱን ፈልጎ የሚመጣው የተገልጋይ ቁጥር ከሆስፒታሉ አቅምና ባለሙያ ጋር አለመመጣጠኑ ችግሩ ጎልቶ እንዲወጣ እንዲባባስ አድርጎታል" ብለዋል። በካርድና መረጃ አያያዝ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ በጤና የመረጃ አያያዝ ስርዓት የሰለጠኑ ከ60 በላይ ባለሙያዎች ቅጥር በመጠናቀቁ በቅርቡ ዘላቂ መፍትሔ ያገኛል ብለዋል፡፡ ሆስፒታሉ ዘመናዊ የካርድና የሕሙማን መረጃ አያያዝ ስርዓት ለመዘርጋት ከ5 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መድቦ የጀመረው ግንባታ በመጠናቀቁ አገልግሎቱ ይሻሻላል የሚል ተስፋ እንዳላቸው አመልክተዋል ። ታካሚውን የሚያመናጭቁና በአግባቡ የማያስተናግዱ ሰራተኞች የአስተሳሰብና የአመለካከት ችግር በመሆኑ የአቅም ግንባታና የግንዛቤ መፍጠሪያ ስልጠናዎች እየተሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ከዚህ ችግር በማይወጡ ባለሙያዎች ላይ  የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድ አመልክተዋል ። "በሆስፒታሉ የሚስተዋለውን የህክምና ክፍል ጥበት ለመቅረፍ ከ350 በላይ አልጋ የሚያስተናግዱና ዘርፈ ብዙ ሕክምና የሚሰጥባቸው  ህንጻዎች ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ ናቸው" ብለዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም