በሀዋሳ የተበላሹ መድሃኒቶች ማክሰሚያ መሳሪያ ለአገልግሎት ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
በሀዋሳ የተበላሹ መድሃኒቶች ማክሰሚያ መሳሪያ ለአገልግሎት ተዘጋጀ
ሀዋሳ ሰኔ 22/2011 በሃዋሳ ከተማ በ51 ሚሊየን ብር የተገነባው የተበላሹ መድኃኒቶች ማክሰሚያ ኢንሲኒሬቴር ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጄንሲ የሃዋሳ ቅርንጫፍ ገለፀ፡፡ የቅርንጫ ጽህፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘመን ለገሰ የዓለም ጤና ድርጅትን ዋቢ አድርገው እንደገለጹት ወደ ሃገር ውስጥ ከሚገቡ መድኃኒቶች መካከል 2 ከመቶ የሚሆኑት የአገልግሎት ጊዜያቸው አልፎ ይበላሻሉ፡፡ የአገልግሎት ጊዜያቸው በማለፉ ለሚወገዱ መድኃኒቶች ዘመናዊ የአወጋገድ ስርዓት ስላልተበጀላቸው በሰው ጤናም ሆነ በአካባቢ ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡ ችግሩ ላለፉት በርካታ ዓመታት በጤናው ዘርፍ ያልተቀረፈ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡ መንግስት የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት በሚወገዱ መድኃኒቶች ውስጥ ያለውን ኬሚካል በከፍተኛ ሙቀት የሚያከስም ኢንሲኒሬተር በሃገሪቱ በ7 ከተሞች በማስገንባት ላይ መሆኑን ጠቁመው የሃዋሳው ተገንብቶ ለአገልግሎት መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ በሃዋሳ ከተማ ወንዶጢቃ በሚባል አካባቢ የተገነባው ይኽው የተበላሹ መድኃኒቶች ማክሰሚያ ከግሎባል ፈንድ በተገኘ 51 ሚሊየን ብር ድጋፍ የተገነባ ሲሆን በ5 ሺህ ካሬ መሬት ላይ ያረፈ ነው ተብሏል ፡፡ "የመድኃኒት ማክሰሚያ ማሽኑም ሙሉ በሙሉ አካባቢን የማይበክልና የእንግሊዝና የአውሮፓ አየር ልቀት ደረጃ / ISO / ፍቃድ ያገኘና ደረጃውን የጠበቀ ነው" ብለዋል፡፡ አቶ ዘመን አንዳሉት ማክሰሚያው ለሚወገዱ መድኃኒቶች ማከማቻ የሚሆን መጋዝን ያለው ሲሆን ለሃዋሳ ከተማና አካባቢዋ ላሉ ጤና ተቋማት አገልግሎት የሚሰጥ ነው ። በመካኒካል ምህንድስና የተመረቀውና የኢንሲኔሬተሩ ባለሙያ የሆነው ወጣት ፍቃዱ ታምራት እንደተናገረው ማሽኑ አዲስ ቴክኖሎጂ የተገጠመለትና በአሁኑ ጊዜ በዘመናዊነቱ ዓለም የሚጠቀምበት ነው፡፡ መሳሪያው ጠጣርና ለአካባቢው ጎጂ የሆኑ ኬሚካሎችን በተለያየ መንገድ የሚያስወግድ ሲሆን ጭሱንም አካባቢን በማይበክል መልኩ እንዲወጣ የሚያደርግ ማጣሪያ የተገጠመለት መሆኑን አስረድቷል ፡፡ የሚወገዱ መድኃኒቶችን ከ900 እስከ እስክ 1ሺህ 300 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በሚደርስ የሙቀት መጠን የማክሰም አቅም እንዳለውም ነው ወጣቱ የተናገረው። የሃዋሳ ከተማ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ቡሪሶ ቡላሾ በበኩላቸው "እስከዛሬ በየጤና ተቋማቱ ተከማችተው የሚገኙት ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶች የሚወገዱበት ስርዓት አስቸጋሪና ደረጃውን የጠበቀ አልነበረም" ብለዋል ፡፡ በሃዋሳ ከተማ የተገነባው የሚወገዱ መድኃኒቶች ማክሰሚያ ኢንሲኒሬተር ከዚህ ቀደም የነበረውን የዘርፉን ችግር የሚቀርፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሃዋሳ ጤና መምሪያ የጤናና ጤና ነክ ግብዓት አቅርቦት ጥራት ቁጥጥር ባለሙያ ሒሩት አሰፋ ከዚህ ቀደም የተበላሹ መድኃኒቶች የሚወገዱበት መንገድ በባለሙያውና በአካባቢው ህብረተሰብ ጤና ላይ ጉዳት ያስከትል እንደነበር አስታውሰው የማሽኑ መተከል ችግሩን እንደሚቀርፈው ገልፀዋል፡፡