ከምሩቃኖቼ 80 በመቶዎቹ የሥራ እድል እንዲያገኙ እየሰራሁ ነው…ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ - ኢዜአ አማርኛ
ከምሩቃኖቼ 80 በመቶዎቹ የሥራ እድል እንዲያገኙ እየሰራሁ ነው…ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ
ሰኔ 21/2011 ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ በየዓመቱ ከሚያስመርቃቸው ተማሪዎች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት የሥራ ዕድል እንዲያገኙ የተቀናጀ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ ። ዩኒቨርሲቲው “ደረጃ ዶትኮም” ከተባለ የመረጃ መረብ ጋር በመተባበር የዘንድሮ ዕጩ ተመራቂዎችንና ቀጣሪ ኩባንያዎችን ያገናኘ የሥራ አውደ-ርዕይ ባለፉት ሁለት ቀናት አካሔዷል ። የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው ባለፉት 66 ዓመታት ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት በመስጠት ከ86 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመርቆ በሀገሪቷ ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ አድርጓል፡፡ የሰለጠነ የሰው ሃይል የማፍራት ተልዕኮውን ከማጠናከር ጎን ለጎን በምርምርና በጥናት ያገኛቸው ውጤቶችና ግኝቶች የማህበረሰቡን ችግር በመፍታት ረገድ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም ባለፉት ሶስት ዓመታት ከዩኒቨርሲቲው የሚመረቁ ባለሙያዎች በፍጥነት የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ከኢንዱስትሪዎችና ከኩባንያዎች ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑንም ምክትል ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል ፡፡ “በተለይ ከደረጃ ዶትኮም ጋር በመተባበር አዳዲስ ሙሩቃን ከቀጣሪዎች ጋር በአካልና በመረጃ መረብ እንዲገናኙ በማድረግ አማራጭ የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው እያደረገ ነው” ብለዋል ። ከሁለት ዓመታት በፊት ከተመረቁት መካከል 79 በመቶ፣ አምና ከተመረቁት ደግሞ 75 በመቶ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው የገለፁት ፕሮፌሰር ንጉሴ ዘንድሮም ከ80 በመቶ በላይ ተመራቂዎች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል ። በዩኒቨርሲቲው የሥራ ተኮር ምክር አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ደጀኔ ገሼ በበኩላቸው “የዩኒቨርሲቲው ምሩቃን በተግባርና በንድፈ ሃሳብ ከሚቀስሙት ዕውቀት በተጨማሪ በገበያው ውስጥ አሸናፊ ሆነው እንዲወጡ መሰረታዊ የኮምፒውተር፣ የቴክኖሎጂና የሥራ ተግባቦት ክህሎቶች ሥልጠና እየተሰጠ ነው” ብለዋል፡፡ የገበያውንና የቀጣሪ ድርጅቶችን ፍላጎት በቀላሉ መረዳት የሚያስችሉ የመረጃ ቋቶችንና ክህሎቶችን የሚያስጨብጡ ስልጠናዎች መሰጠቱንም ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው ያስመረቃቸው ባለሙያዎች የሥራ ዕድል ማግኘት ያልቻሉባቸውን መሰረታዊ ክፍተቶች በመከታተል በቀጣይነት እንዲስተካከሉ የሚረዳ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል ። በዓውደ-ርእዩ ላይ የዩኒቨርሲቲው ዕጩ ተመራቂዎች ከድሬዳዋና ከአዲስ አበባ ከተመረጡ 17 ፋብሪካዎች ጋር እንዲገናኙና የስራ እድል የሚያገኙበት አማራጭ እንዲሰፋ መደረጉን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል ። ከዓውደ-ርእዩ ተሳታፊዎች መካከል በሞኢንኮ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ የፋይናንስና አስተዳደር ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ቦጋለ እንደገለፁት መሰል የሥራ አውድ-ርዕይ መዘጋጀቱ ድርጅቱ በፋይናንስና በመካኒካል ምህንድስና የተመረቁ አዳዲስ ባለሙያዎችን በቀላሉ ለመቅጠር ያስችላል ። “እድሉን በመጠቀም ደግሞ ከወዲሁ ምልመላና ምዝገባ አካሂደናል” ብለዋል፡፡ “የዘንድሮው የእርሻ ምጣኔ ሃብት ዕጩ ተመራቂ አያሌው ገመቹ በበኩሉ አውደ ርዕዩ አዳዲስ ተመራቂዎች የሥራ ዕድል የሚያገኙበትን መንገድ የሚያመቻች በመሆኑ የሚበረታታ ነው” ብሏል ፡፡ ”ይህ አጋጣሚ የሥራ እድል ማግኘት ያስችላል።ያገኘነውን ስልጠና ደግሞ ገበያው ምን እንደሚፈልግ ያስገነዘበን በመሆኑ ሳንቸገር የቀጣሪዎችን በር በማንኳኳት ስራ እንደምናገናኝ እርግጠኛ ነኝ” የሚል አስተያየት ሰጥቷል ፡፡ ለሁለት ቀናት ተካሔዶ ትናንት ማታ ከተጠናቀቀው አውደ ርዕይ ጎን ለጎን ሁሉም የትምህርት ክፍሎች የተሳተፉበት የትምህርት ጥራትን ማሻሻል በሚያስችሉ ጉዳዮችና በተቀጣሪዎች በኩል በሚታዩ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ላይ ያነጣጠረ የፓናል ውይይት ተካሔዷል፡፡