ዩኒቨርሲቲው የልህቀት ማዕከሉን በአገረሰብ ዕውቀቶችና ግብርና ላይ አድርጎ የማህበረሰብ አገልግሎት እየሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው የልህቀት ማዕከሉን በአገረሰብ ዕውቀቶችና ግብርና ላይ አድርጎ የማህበረሰብ አገልግሎት እየሰጠ ነው

አዲስ አበባ ሰኔ 2/2010 የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የልህቀት ማዕከሉን በአገረሰብ ዕውቀቶችና ግብርና ላይ አድርጓል፤ 'የማህበረሰብ አገልግሎቱም በዚሁ መስክ የተቃኘ ነው' ብሏል። የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሲሳይ ሸዋአማረ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ከተመሰረተ ሰባት ዓመታትን ያስቆጠረው ዩኒቨርሲቲው፤ የልህቀት ማዕከሉን በአገር በቀል ዕውቀትና በግብርና ጥበበ ሕይወት ላይ አድርጓል። 'እንደማንኛውም ዩኒቨርሲቲ ከአካዳሚክ ትምህርቶች በተጨማሪ በምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ላይ መሰማራቱን ገልጸው፤ ዩኒቨርሲቲው ባለበት አካባቢ በሚገኙ አገር በቀል ዕውቀቶች ላይ ምርምር እያደረገ ነው' ብለዋል። በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ ከሚታወቁ አገር በቀል ዕውቀቶች ውስጥ 'የአንትሮሽት' የእናቶች ቀን ባህል፣ የማኅበረሰቡ የቤት አሰራር ጥበብ፣ የ'ጀፎረ' የመንደር ምስረታ፣ የ'ቂጫ' የዳኝነት ስርዓትና መሰል አገረሰባዊ ዕውቀቶች ላይ ማህበራዊ ጥናትና የማስተዋወቅ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። 'አንትሮሽት' በማህበረሰቡ ዘንድ ከ300 ዓመታት በላይ የቆየ በየዓመቱ ለእናቶች ክብርና ምስጋና ለማቅረብ የሚከበር ባህል ሲሆን የ'ቂጫ' ዳኝነት ደግሞ ማህበረሰቡ የተጋጩ ሰዎችን ግጭት የሚፈታበት ስርዓት ነው። እንዲሁም 'ጀፎረ' ቤቶችን በ60 ሜትር ርቀት የመገንባትና አካባቢውን አስውቦ ለአፈርና አካባቢ ጥበቃ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው የመንደር ምስረታ ስርዓት ነው። በ19ኛው ክፍለ ዘመን ለአካባቢው ሴቶች እኩልነት የታገለች ኢትዮጵያዊት 'የቃቄ ውርድወት' የተባለች ጀግና እንስት በጉራጌ ማኅበረሰብ ውስጥ እንደነበረች ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው እነዚህና ሌሎች አገረሰባዊ ዕውቀቶች እንዳይጠፉና ተምሳሌት እንዲሆኑ አጥንቶ የማሳተምና የማስተዋወቅ ስራዎችን እያከናወነ እንደሆነ ዶክተር ሲሳይ ተናግረዋል። በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ወረዳዎች የግብርና የምርምር ጣቢያዎች አቋቁሞ፤ በቡና፣ በሙዝ፣ በእንሰት፣ በፖምና ለደን ልማት ለሚያገለግሉ አገር በቀል ተክሎች ላይ ምርምር እያደረገ ነው። የግብርና ጥበበ ሕይወት ወይም ባዮቴክኖሎጂ የዩኒቨርሲቲው አንዱ የልህቀት ማዕከል መሆኑን ገልጸው፤ ከነዚህ መካከል በተለያዩ የአየር ንብረት ክልሎች ለደን ሽፋን የሚውሉ ችግኞችን በማባዛትና ለአካባቢው ማህበረሰብ የማሰራጨት ስራዎችን እያከናወነ እንደሆነ ጠቁመዋል። ከነዚህም ውስጥ በየዓመቱ ከ100ሺህ በላይ አገር በቀል ችግኞችን አልምቶ በነጻ ሲያከፋፍል የቆዬ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህ ዓመትም ከ130ሺህ በላይ የቡናና የደን ሽፋን የሚውሉ ችግኞችን በነጻ አባዝቶ እንደሚሰጥ ተናግረዋል። በሌላ በኩል በአካባቢው በስፋት የሚታወቀውን የእንሰት ተክል ምርታማነትና ጥራት ለማሳደግ ከሚደረጉ ምርምሮች በተጨማሪ ሙዝና አፕል በመሳሰሉ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በምርምር በመለየት በባዮ ቴክኖሎጂ አባዝቶ ለማሰራጨት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ይህም ማህበረሰቡ ከምግብ ወደ ገበያ መር የግብርና ምርቶች እንዲለወጥና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱ እንዲጎለብት በማድረግ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ማምጣቱን ጠቅሰዋል። ዩኒቨርሲቲው ከሆለታ የግብርና ምርምር ማዕከል ጋር በመሆን በአካባቢው የሚገኙ የተሻሻሉ የወተትና የስጋ ምርት ያላቸውን ከብቶች ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ዝርያ ለይቶ የማዳቀል ስራ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል። በአካባቢው በተደረገ ጥናት መሰረት የስጋና ወተት ምርታማነት ከ10 በመቶ በታች እንደሆነ ገልጸው፤ በተደረጉ የማዳቀል ስራዎች እስካሁን መገኘት ከሚገባው 50 በመቶ የስጋና ወተት ምርት ማድረስ መቻሉን ለአብነት አንስተዋል። የዩኒቨርሲቲው የምርምር ዳይሬክተር አቶ አድማስ ብርሃኑ ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ ትምህርት ክፍሎች የተውጣጡ ተመራማሪዎች በአንድ ጉዳይ ላይ ምርምር የሚያደርጉበት 'የውስጣዊና ተሸጋጋሪ የምርምር ፍልስፍና' የሚከተል አሰራር እንደሚተገብር ገልጸዋል። በቅንጅት ምርምር ማካሄዱ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በአጭር ጊዜና በቀላሉ ለመፍታት ዕድል የሚሰጥ እንደሆነ ጠቁመዋል። የምርምር ጣቢያዎቹ ከዩኒቨርሲቲው በርቀት ላይ እንደሚገኙ ገልጸው፤ ዩኒቨርሲቲው ታዳጊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተሽከርካሪና ሎጀትስቲክስ እንዲሁም የፋይናስ ድጋፍ እጥረት ችግሮች እንዳሉበት ገልጸዋል።