ባለፉት ዓመታት የታዩ የበጀት ችግሮች በቀጣዩ በጀት ዓመትም እንዳይደገሙ መስራት ይገባል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ዓመታት የታዩ የበጀት ችግሮች በቀጣዩ በጀት ዓመትም እንዳይደገሙ መስራት ይገባል ተባለ
አዲስ አበባ ሰኔ 21/2011 በቀደሙት ዓመታት የታዩ የበጀት ክፍተቶች በቀጣዩ ዓመት እንዳይደገም መስራት እንደሚገባ የገቢ ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ። የገንዘብ ሚኒስቴር በበኩሉ የበጀት ረቂቁ ሲዘጋጅ ችግሮቹን ለመመለስ ታሳቢ ተደርጓል ብሏል። ማሳሰቢያው የተሰጠው በ2012 ዓም የፌደራል መንግስት በጀት ረቂቁ ላይ የህዝብ አስተያየት እንዲሰጥበት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በተወያየበት ወቅት ነው። በዚሁ ወቅት ቋሚ ኮሚቴው እንዳለው ባለፉት ዓመታት የክልሎች ፍትሃዊ የበጀት ክፍፍል ፣ የበጀት እቅድና ዝግጅት አለመጣጣም፣ የፕሮጀክቶች አዋጭነት ጥናት፣ የአስፈጻሚ አካላትና የቁጥጥር ስርዓት ላይ ችግሮች ነበሩ። በዚህም የክልሎች የበጀት ክፍፍል ፍትሃዊነት ጥያቄ ለፌደራሊዝም ስርዓት ስጋት ፈጥሯል ብሏል። ፕሮጀክቶች በበጀት እጥረት በተያዘላቸው ጊዜ አይጠናቀቁም፣ ይህን ተከትሎ በቁጥጥር ችግርና በአስፈጻሚዎች ድክመት የበጀት ጉድለት ማስከተሉን ቋሚ ኮሚቴው አስታውቋል። ለተነሱት ጉዳዮች ምላሽ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ “ረቂቁን ስናዘጋጅ የሚቀጥለው ዓመት እቅዶች ምንድን ናቸው?፣ አጠቃላይ የአገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም ምን እንደሚመስልና ቀጣይ ሊሰሩ የሚገባቸውን ጉዳዮች በዝርዝር በመለየት ነው።” ብለዋል። በጀቱ የተዘጋጀው ወጥ የሆነ የደመወዝ ማስተካከያን በሂደት ለመመለስ፣ የኢኮኖሚውን ዕድገት እና የተያዘውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዶችና ቀጣይነት ያለውን ልማት ታሳቢ በማድረግ መሆኑንም ዶክተር እዮብ ተናግረዋል። ዶክተር እዮብ አያይዘውም አጠቃላይ የመንግስት ወጪ ከገቢው ይበልጣል ተብሎ በመታሰቡ ከውጭ በእርዳታ የሚገኘውን ገንዘብ ከበጀቱ ጋር ታሳቢ መደረጉንም አመልክተዋል። የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግርን ለመቀነስ ለፕሮጀክቶች ግብዓት ለሚሆኑ አገራዊ ፕሮጀክቶች ቅድሚያ እንዲሰጥ ከብሔራዊ ባንክ ጋር በጋራ እንደሚሰራም ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል። የተቋማትና የፕሮጀክቶች አስተዳደር ችግርን ለመከላከል የሚያስችል ስርዓት ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ጀምሮ እስከ ታች ድረስ ይዘረጋል ሲሉም ገልጸዋል። ገቢ ከሌለ ወጪ የለም ያሉት ደግሞ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ለምለም ሓድጉ፤ "የአገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብ የዜግነት ግዴታ" ነው ብለዋል። ችግሩ የመነጨው የአገሪቱ ገቢን የመሰብሰብ አቅም ደካማ በመሆኑ እንጂ በአገሪቱ በርካታ የገቢ ምንጭ መኖሩን ጠቅሰዋል። በመሆኑም የገቢ አሰባሰቡ ትኩረት እንደሚሻ በውይይቱ ላይ ተመልክቷል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሚቀጥለው ዓመት የቀረበውን የ387 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት ረቂቅ ላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል። የቀጣዩ አመት በጀት በዚህ አመት ከነበረው በጀት የ1 ነጥብ 6 በመቶ ጭማሪ አለው። ኢኮኖሚው በሚቀጥለው የበጀት ዓመት የተወሰነ መነቃቃት በማሳየት ከዘጠኝ በመቶ በላይ እድገት እንደሚያስመዘግብ ታምኖበታል። የበጀት ረቂቁ ሰኔ 25 ቀን 2011 ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት ሰኔ 27 ቀን 2011 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚጸድቅ ይጠበቃል።