ወጣቱ ትውልድ አገርና ሕዝብን በማስቀደም ሰላምና አንድነትን ማስጠበቅ አለበት--የሃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቱ ትውልድ አገርና ሕዝብን በማስቀደም ሰላምና አንድነትን ማስጠበቅ አለበት--የሃይማኖት አባቶች
መቀሌ ሰኔ 21/2011 ወጣቱ ትውልድ አገርና ሕዝብን በማስቀደም የአገሪቱን ሰላምና አንድነት እንዲያስጠብቅ የትግራይ ክልል የሃይማኖት አባቶች አስገነዘቡ። የሃይማኖት አባቶች ለኢዜአ እንደገለጹት ወጣቱ ከጄኔራል መኮንኖቹና ከአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች የዓላማ ፅናት በመማር አገርንና ሕዝብን ማስቀደም አለበት። የመቀሌ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን አባ ጥዑም በርኼ ወጣቱ ከቤተሰቦቹና ከግል ጥቅማቸው አገርን በማስቀደም መስዋዕት ከሆኑት ከፍተኛ አመራሮች የዓላማ ጥናትን ሊማር እንደሚገባ አመልክተዋል። ግድያው የሕግ የባላይነትን በማስከበር ሂደት ያለውን ክፍተት አንደሚያሳይ የጠቆሙት አባ ጥዑም የድርጊቱን ፈጻሚዎች መንግሥት በአስቸኳይ አጣርቶ ለሕዝቡ እንዲያሳውቅና በሕግ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል። ድርጊቱ" የሰውን ልጅ አትግደል" የሚለው ሃይማኖታዊ ትዕዛዝ የሚጻረር ከመሆኑም በላይ፤ የአገሪቱን መልካም ገጽታ እንደሚያበላሽ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን ኅብረት ተወካይ አቶ ደሳለኝ ባራኪ በበኩላቸው ሕይወታቸውን ለአገር አንድነትና ሉዓላዊነት ከሰሩት የጦር መኮንኖች ሕይወት ወጣቱ አገሩንና ሕዝቡን እንዲያፈቅር ያስችለዋል ብለዋል። የመካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያንን የወከሉት ቄስ በሪሁ ከበደ ወጣቱ ትውልድ አገርና ህዝብ ሁሌም ነዋሪ መሆናቸው በመገንዘብ የአገሪቱን እድገትና ሰላም እንዲያስቀጥል ጠይቀዋል። ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የመጡት መልክአገነት አባ ሃብተማሪያም ወረስ በበኩላቸው ወጣቱ ለአገራቸው ሰላምና ለሕዝቦች እኩልነት የሰሩት ጀግኖች ፈለግ መከተል ይገባዋል ብለዋል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትን በመወከል አስተያየታቸውን የሰጡት ሼህ መሐመድ አሚን ሙስጠፋ በበኩላቸው ወጣቱ ከፍተኛ አመራሮች የከፈሉትን መሰዋዕት ትርጉም በመረዳት ሥራቸውን እንዲያስቀጥል አሳስበዋል።