ቀጥታ፡

የጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ሃኪሞች ከቻይና ከመጡ የህክምና ልዑክ ጋር በመሆን የነጻ ህክምና አገልግሎት ሰጡ

ሰኔ 21/2011 የጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ሃኪሞች ከቻይና ሁናን ግዛት ህዝቦች ሆስፒታል ሃኪሞች ልዑክ ጋር በመተባበር በቃሊቲ አረጋውያን እንክብካቤ ማዕከል ነጻ የህክምና አገልግሎት ሰጡ። ''በእድሜ ብዛት ለከባድ በሽታዎች ለሚጋለጡ በማዕከሉ የተጠለሉ አረጋውያን ህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ነው'' ብሏል ማዕከሉ። የጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ሀኪሞች ከቻይና የ'ሁናን ግዛት ህዝቦች ሆስፒታል' ሀኪሞች ቡድን ጋር በመሆን በቃሊቲ የአረጋዊያን መጦሪያ ማዕከል የበጎ ፈቃድ የህክምና አገልግሎት ሰጥተዋል። ቻይና በኢትዮጵያ ውስጥ ከምታደርገው የህክምና ድጋፍ ፕሮጀክቶች መካከል ከ45 ዓመታት በፊት ጀምሮ ሃኪሞችን በተለያየ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ እየላከች የምትሰጠው ነጻ የህክምና አገልግሎት ይገኝበታል። በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ 'የኢትዮ ቻይና ወዳጅነት ሆስፒታል' በሚል ስም ከስምንት ዓመታት በፊት ተመስርቶ እ.ኤ.አ ከ2008 ጀምሮ በአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ስም 'ጥሩነሽ ቤጂንግ' በሚል ስያሜ በተቀየረው ሆስፒታል የቻይና ሃኪሞች በቋሚነት የሚሰሩበትና ልዩ እርዳታ የሚያደርግለት ተቋም ነው። በተለያዩ ጊዜ የህክምና ልዑክ እየመጣ በቻይና ቤጂንግ ሆስፒታል ነጻ የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ዘንድሮም ለ21ኛ ዙር 16 አባላት ቡድን የአንድ ዓመት የህክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። ከዚህም በተጨማሪ ለአንድ ወር የህክምና ድጋፍ ለማድረግ የቻይና ሁናን ግዛት ህዝቦች ሆስፒታል ሃኪሞች ቡድን በሆስፒታሉ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ የቡድኑ መሪ ዶክተር ያንግ ዣይ ይናገራሉ። ከባለሙያዎች መምጣት ባሻገርም የሆስፒታሉ የህክምና ማዕከላት ባለሙያዎች በቻይና የአጫጭር የህክምና ሙያ ስልጠናና ጉብኝቶች ተካፋይ እንዲሆኑ ይደረጋል። በዛሬው ዕለት ደግሞ ሃኪሞቹ ከጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ባለሙያዎች ጋር በመሆን ጋር በበጎ አድራጎት ስራ ቃሊቲ በሚገኘው የአረጋውያን እንክብካቤ ማዕከል የነጻ ምርመራ አገልግሎት ሰጥተዋል። ልዑኩ በተለያየ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ሆስፒታሎች ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸው፤ ከሰሞኑም አንድ ሚሊዮን ብር የሚገመት የህክምና ቁሳቁሶችን ለሆስፒታሉ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል። የጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ጅብሪል አባስ የበጎ አድራጎት ወር ተብሎ በአገር አቀፍ ደረጃ የታወጀውን ጥሪ ተከትሎ የሆፒታሉ ሰራተኞች በአረጋውያኑ መጦሪያ ማዕከል ነጻ የጤና አገልግሎት ለመስጠት መገኘታቸውን ተናግረዋል። ''ከቻይና ከመጡ የሃኪሞች ቡድን አባላት ከጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ሃኪሞች ጋር በመሆን በበጎ አድራጎት ስራው ለመሳተፍ በመፈለጋቸው ለአረጋውያኑ ነጻ የህክምና ምርመራ እያደረጉ ነው'' ብለዋል። ከዚህ በፊት የሆስፒታሉ ባለሙያዎች በማዕከሉ በመገኘት የበጎ አድራጎት ስራዎች ሲያከናውኑ እንደነበር ገልጸው፤ ከቻይና ከመጡ የህክምና ስፔሻሊስቶች ጋር በመሆን የተዘጋጀው የህክምና ፕሮግራም አገልግሎቱን የሚያጠናክር አጋጣሚ መሆኑን አመልክተዋል። የነጻ ምርመራው ዓላማ በማዕከሉ የተጠለሉ አረጋውያን በደም ግፊት፣ የአዕምሮ፣ የልብ፣ የስኳርና ተያያዥ ህመሞች ስለሚጋለጡ ምርመራ አድርጎ በቀጣይ የህክምና ድጋፍ ለማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል። የቃሊቲ አረጋውያን እንክብካቤ ማዕከል ስራ አስኪያጅ አቶ ጥላሁን ከበደ በ1962 ዓ.ም የተመሰረተው ማዕከሉ በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ስር ሆኖ 169 አረጋውያንን አስጠልሏል። ተቋሙ ከጎዳና የተሰባሰቡ አረጋውያን የመጠለያ፣ የምግብ፣ የንጽህና፣ የምክር፣ የህክምናና ሌሎች አገልግሎቶች እንደሚሰጥ ገልጸዋል። ብዙዎቹ አልጋ ላይ የሚገኙ ከእድሜ ጋር በተያያዘ ለደም ግፊት፣ ስኳር፣ የልብና ሌሎች ከፍተኛ ህክምና የሚጠይቁ በሽታዎች የተጋለጡ መሆናቸውን ገልጸው፤ ''በዕለቱ በሃኪሞች ቡድን የተደረገው ጉብኝትና ድጋፍም መልካም አጋጣሚ ነው'' ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም