ቀጥታ፡

የመገናኛ ብዙሃን በዜጎች መካከል የመተማመን ስሜትን በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ላይ በትኩረት መስራት አለባቸው ተባለ

አዲስ አበባ ሰኔ 21/2011 የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን በዜጎች መካከል የመተማመንና የመግባባት ስሜትን በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ላይ በትኩረት በመስራት ሃገራዊ አንድነትን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ አንድ የስነ-ልቦና ባለሙያ ተናገሩ። ሰሞኑን በባህርዳርና አዲስ አበባ የተፈፀመው የከፍተኛ ባለስልጣናት ግድያ ችግሮችን በውይይት መፍታት ካለመቻል የመነጨ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ። የስነ-ልቦና ባለሙያው አቶ ነጋሽ አበበ ለኢዜአ እንደገለጹትም በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ስምምነት አለመኖርና እርስ በእርስ አለመተማመን መጠፋፋትን ጨምሮ ለተለያዩ ቀውሶች ይዳርጋል ብለዋል። የስነ-ልቦና ባለሙያው አክለውም በተፈጠረው ችግር ህብረተሰቡ እኩል በአንድ ላይ ማዘኑ እና መጨነቁ እርስ በርስ ያለውን መተሳሰብ የሚያሳይ ነው፤ ይህም ችግሩን ትተን ወደፊት ማየት ከተቻለ ይሄን ችግር ማለፍ የማያቅተን መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡ ይህ ጥቃት ሁሉንም ያሳዘነና ያስከፋ፤ ወንድም በወንድሙ ላይ ስጋት እንዲይዘው፤ በእያንዳንዱ ማህበራዊ ህይወት ላይ አለመተማመንን ሊፈጥር የሚችል ነው ያሉት ባለሙያው ነገር ግን እያንዳንዱ የህይወት መስተጋብር በደንብ ከተመረመረ የምንጠረጥረው ሳይሆን የምናምነው ይበዛል ብለዋል። በመሆኑም ያልተጣራ መረጃን ይዞ ከመቀባበል ይልቅ በጎ ነገር ላይ በመወያየት ዘላቂ የሆነ ሰላምን ማምጣት ይቻላል የሚሉት አቶ ነጋሽ  የመገናኛ ብዙሃን በዚህ ረገድ ያለባቸው ኀላፊነት ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም