ኢዜአ በአገራዊ ለውጥ ላይ ህዝቡ የሚፈልጋቸውን ዘገባዎች አጠናክሮ እንዲቀጥል ምክር ቤቱ አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜአ በአገራዊ ለውጥ ላይ ህዝቡ የሚፈልጋቸውን ዘገባዎች አጠናክሮ እንዲቀጥል ምክር ቤቱ አሳሰበ
ሰኔ 21/2011 የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤንጀሲ (ኢዜአ) በአገራዊ ለውጥ ላይ ህዝቡ የሚፈልጋቸውና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን በመለየት ለህብረተሰቡ የሚያደርሰውን መረጃ አጠናክሮ እንዲቀጥል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ። ኤጀንሲው የ2011 በጀት አመት የ11 ወር እቅድ አፈጻጸሙን በምክር ቤቱ ለህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ አቅርቧል። የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ በቀለ ሙለታ በ11 ወራት ውስጥ በዜና እና ዜና ነክ ታቅደው የተከናወኑ ተግባራትን የተመለከተ ሪፖርት አቅርበዋል። ቋሚ ኮሚቴው በቀረበው ሪፖርት ላይ በጥንካሬና በድክመት የገመገማቸውን ነጥቦች አንስቷል። ተቋሙ አቅሙን ለማጠናከር ከአገር ውስጥና ውጪ የወሰዳቸው ልምዶች እንዲሁም ሙያተኞችን ለማብቃት ያደረገውን ጥረት በጠንካራ ጎን አይቶታል። ለአብነት ከአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ በግጭት ዘገባ፣ በሰላም ጋዜጠኝነት፣ ሃሰተኛና አሳሳች ዜናዎችን ከትክክለኛ ዜና መለየት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ለሙያተኞች የሰጠውን ስልጠና ጠንካራ ጎን መሆኑን ገልጿል። ኤጀንሲው በአገራዊ ለውጥ ላይ ህዝቡ የሚፈልገውን መረጃና ትኩረት የሚያሻቸው የመልካም አስተዳደር ችግርን የተመለከቱ ዜናዎችን በመስራት በኩል የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል። የሚዲያ የለውጥ ሰራዊት ግንባታ ለማደራጀት የተከናወኑ ተግባራት ቢኖሩም የቡድኖችን አቅም በማጠናከር በቀጣይ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው አንስቷል። ተቋሙ የሚያከናውናቸው የተለያዩ ጥናቶች ያመጡትን ለውጥ መገምገም፣ ለክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የሚደረገውን ድጋፍ ማጠናከርና ሌሎች ትኩረት የሚሹ ተብለው የተለዩ ጉዳዮች በቋሚ ኮሚቴው ተነስተዋል። ከሰራተኛ ፍልሰት፣ ከግዥ መዘግየትና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎች ከቋሚ ኮሚቴው ተነስተው ከሃላፊዎች ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል። ኢዜአ በ12 ወራት ውስጥ 12 ሺህ ዜናዎችን ለመስራት አቅዶ በበጀት ዓመቱ እስካሁን ከ13 ሺህ 5 መቶ በላይ ዜናዎችን መስራት ችሏል።