በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ''ኦነግ ሸኔ በሚል ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ሽፍቶች"ን የሚያወግዝ ሰልፍ ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ''ኦነግ ሸኔ በሚል ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ሽፍቶች"ን የሚያወግዝ ሰልፍ ተካሄደ

አዲስ አበባ ሰኔ 21/2011 በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ በመውጣት ''ኦነግ ሸኔ በሚል ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ሽፍቶች" በህዝብ ላይ እየፈጸሙ ያለውን ግፍ እንደሚያወግዙ አስታወቁ። በኦሮሚያ ክልል በደንቢ ዶሎ ፣ በጊምቢ፣ በቦረና ትናንት በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ነዋሪዎቹ ለ'ኦሮሞ ህዝብ ነጻነት እታገላለሁ' በማለት ጫካ በመግባት "ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ሽፍቶች"ን እንደሚያወግዙ በተለያዩ መፈክሮቻቸው ገልጸዋል። ነዋሪዎቹ የተቃውሞ ሰልፍ እንዲያካሂዱ ያስገደዳቸው ጉዳይ የህግ የበላይነት እንዲከበር ለማሳሰብና 'ሸኔ ኦነግ' በሚል "ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ሽፍቶች"ለማውገዝ ነው። ነዋሪዎቹ እንደገለጹት ፤ በጥፋት ቡድኑ የተነሳ የክረምት ወቅት የእርሻ ስራቸውን ለማከናወን አልቻሉም ፤ የንግድ ስራቸውንም ለመስራት ተቸግረዋል ፤ መንግስት ሰላምን የማረጋገጥና የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ተግባሩን እንዲወጣ ጠይቀዋል። "ሸኔ ኦነግ" የተሰኘው የታጠቀ ሽፍታ ጥቃት ይፈጽምብናል'" በሚል ከፍተኛ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ያመለከቱት ሰልፈኞቹ፤ ቡድኑ የእለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን እንዳያደናቅፍ መንግስት ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል። ''የኦሮሞ ህዝብ ለበርካታ ዓመታት በመታገል ያገኘውን ድል በጥፋት ቡድኑ መበላሸት የለበትም'' ያሉት የተቃውሞ ሰልፈኞቹ ፤ ለአገር የሚሰሩ ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያ ፎቶአቸው እየተለጠፈ ስማቸው መጥፋቱ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል። ሰልፈኞቹ የመንግስት አመራር አባላት ፣ መደበኛ ፖሊሶች እንዲሁም የፍርድ ቤት ሰራተኞች ወደ መደበኛ ስራቸው እንዲገቡም ጥሪ አቅርበዋል። የአካባቢያቸውን ሰላም በራሳቸው ለመጠበቅ ፣ ሰላምና ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ነው የገለጹት። መንግስት ከህዝብ ፍላጎት አፈንግጠው በህገወጥ ድርጊት ውስጥ የሚሳተፉ አካላት ላይ እርምጃ በመውሰድ የህግ የበላይነትን እንዲያረጋግጥ የጠየቁት ሰልፈኞቹ ፤ ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙና ህዝብን የሚዘርፉና ጥቃት የሚያደርሱ አካላትን እንደሚታገሉ አረጋግጠዋል። ተቃውሟቸውን በሰልፍ የገለጹት ነዋሪዎች 'ሸኔ ኦነግ' በመባል የሚታወቀው ቡድን ሽፍታ እንደሆነም ተናግረዋል። ህዝብን የሚዘርፍ፣ የሚገድልና የሚያቆስል ቡድን ከሽፍታ ተለይቶ እንደማይታይ ተናግረዋል። ለተቃውሞ ሰልፍ አደባባይ የወጡት ነዋሪዎች "ሸኔ ኦነግ" የተባለው ቡድን የሚወስደውን እርምጃ በማውገዝ የኦሮሞን ህዝብ እንደማይወክልም አስታውቀዋል። ግንቦት 21 ቀን 2011 ዓ.ም ኦነግ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እና እርቀ ሰላም ኮሚቴ ጋር በሰጠው መግለጫ ፤ የታጠቀ ሰራዊት እንደሌለው ማረጋገጡ ይተወሳል። ኦነግ አገሪቷ በለውጥ ሂደት ውስጥ በገባችበት ወቅት ሁሉም ተቃዋሚ ሀይሎች በሰላማዊ መንገድ መታገል እንደሚችል ተገልጾ በመንግስት ጥሪ ከተደረገ በኋላ ወደ አገር ቤት ተመልሷል። የቄለም ወለጋ፣ የምዕራብና ምስራቅ ወለጋ እንዲሁም ቡኖ በደሌ የተለያዩ ወረዳዎች ነዋሪዎቹ ''የኦሮሞን ህዝብ ነጻ አወጣለሁ'' በማለት ጫካ የገባ ማንኛውም ቡድን እንደማይወክላቸው የተቃውሞ ሰልፍ ማካሄዳቸውን ከትናንት በስቲያ ዘግበናል። በተያያዘም ሰልፈኞቹ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና በአዲስ አበባ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ላይ የተፈጸመውን ግድያ አውግዘው ድርጊቱ በአገሪቷ የመጣውን ለውጥ ለመቀልበስ የተደረገ ሙከራ በመሆኑ አጥብቀው እንደሚቃወሙት ተናግረዋል።