አትሌቶች በአበረታች መድሃኒት ሳቢያ የአገሪቱን ስም ማጉደፍ የለባቸውም ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
አትሌቶች በአበረታች መድሃኒት ሳቢያ የአገሪቱን ስም ማጉደፍ የለባቸውም ተባለ
አዲስ አበባ ሰኔ 2/2010 አትሌቶች ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ስኬት ማስቀጠል እንጂ በአበረታች መድሃኒት ምክንያት የአገሪቱን ስም ማጉደፍ የለባቸውም ተባለ። የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች መድሃኒት ጽህፈት ቤት እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በጋራ በመሆን ለአትሌት የማናጀር ወኪሎችና ለታዋቂ አትሌቶች በአበረታች መድሃኒት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥተዋል። በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር አያሌው ጥላሁን በስልጠናው ላይ እንደተናገሩት "በቅርብ ጊዜ እየታየ ያለው የአትሌቶች ችግር ማሸነፍን ብቻ መፈለግ ነው"። በመሆኑም አስተሳሰብን ማስተካከል ያስፈልጋል ያሉት ባለሙያው ብዙ ልምምድ ሳይሰሩ ቶሎ ውጤት መሻት እንደማይገባም አስገንዝበዋል። "በአንድ ጊዜ አሸናፊነትን ከመፈለግ ይልቅ በጊዜ ሂደት ማሸነፍ እንደሚቻል ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል" ነው ያሉት። "በታሪካችን በአትሌትክሱ ዘርፍ የነበረውን ህዳሴ ማስቀጥል እንጂ የአገሪቱን ስም ባልተገባ መልኩ ማስነሳት አይገባም" ሲሉም ተናገረዋል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴም አበረታች መድሀኒት ላይ በብዛት ችግር ፈጣሪዎች በፌዴሬሽኑ ዕውቅና በሌላቸው ማናጀሮች በኩል የሚወዳደሩ አትሌቶች መሆናቸውን ገልጿል። ሆኖም ችግሩ ሲከሰት የሁሉን አትሌቶች ስም በማጉደፉ ችግሩን በጋራ መከላከል እንደሚገባ አስገንዝቧል። "አበረታች መድሃኒት የወሰዱ አትሌቶች ላይ እርምጃ የሚወሰደው ንጹሃን አትሌቶችን ለማዳን እንጂ ማንንም ለመጉዳት አይደለም" ብሏል። የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች መድሃኒት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ይደርሳል "አበረታች መድሃኒት ወስደዋል ተብለው ከተቀጡ አትሌቶች አብዛኞቹ ሆነ ብለው የሚወስዱ ናቸው" ብለዋል። አበረታች መድሃኒት የተገኘባቸው አትሌቶች በመጀመሪያ እስከ አራት ዓመት ከስፖርታዊ ውድድር እንዲርቁ ሲደረግ በተደጋጋሚ ወስደው የሚገኙ አትሌት ላይ ደግሞ እስከ እድሜ ልክ እገዳ ይጠብቃቸዋል፤ በወንጀልም ይጠየቃሉ። በኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ውጤታቸው ታይቶ መድሃኒቱን ወስዳችኋል የተባሉ አምስት አትሌቶች እስከ አራት ዓመት የሚደርስ ቅጣትና በውድድሩ እንዳይሳተፉ እገዳ ተላልፎባቸዋል።