የመቐለ ሰብዓ አንደርታ እና የደቡብ ፖሊስ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የመቐለ ሰብዓ አንደርታ እና የደቡብ ፖሊስ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ይካሄዳል
ሰኔ 21/2011 የመቐለ ሰብዓ አንደርታ እና የደቡብ ፖሊስ የ28ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በወጣው መርሃ ግብር መሰረት ይካሄዳል። የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ሰኔ 16 ቀን 2011 ዓ.ም መካሄድ የነበረበት ቢሆንም በወቅቱ አዲስ አበባ እና በባህርዳር በነበረው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ጨዋታው ሳይካሄድ ለሌላ ጊዜ መራዘሙ ይታወቃል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተራዘመው ጨዋታ ሰኔ 22 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲካሄድ መርሃ ግብር ቢያወጣም የደቡብ ፖሊስ እግር ኳስ ክለብ ጨዋታውን በፋይናንስ ችግር ምክንያት መቐለ ሄዶ ለመጫወት እንደማይችል ለፌዴሬሽኑ ገልጾ ነበር። "መቐለ ከደረስን በኋላ ፌዴሬሽኑ ጨዋታው ተራዝሟል ወደ መጣችሁበት ተመለሱ ባለው መሰረት ወደ ሀዋሳ ተመልሰናል" ሲሉ የክለቡ ስራ አስኪያጅ ምክትል ኮማንደር ግርማ ዳባ ለኢዜአ ገልጸዋል። ጨዋታው በመራዘሙ ምክንያት ክለቡ ያለአግባብ ወጪ በማውጣቱ በድጋሚ ሄዶ ጨዋታውን ለማካሄድ የበጀት ችግር በመግጠሙ ምክንያት ለእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ወጪያቸውን እንዲሸፍን መጠየቃቸውን ተናግረዋል። ከእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የስራ ሃላፊዎች ጋር በተደረገው የስልክ ውይይት ክለቡ ወደውድድሩ ስፍራ እንዲያቀና፤ የፌደሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተሰብስቦ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ እንደሚሳልፍ ነግረውናል ብለዋል። ክለቡም የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ተቋም በመሆኑ 'አይዋሸንም ብለን በማመን' ተጫዋቾቹ ትናንት ከምሽቱ አንድ ሰአት መቐለ መግባታቸውን አመልክተዋል። በ30ኛው ሳምንት ወደጅማ በመሄድ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ለሚያደረግው ጨዋታ ያዘጋጀውን በጀት ለድጋሚ የመቐለ ጉዞ ማውጣቱንና ወደ ጅማ ሄዶ ለመጫወት የሚያስችል በጀት ክለቡ እንደሌለውም ነው ምክትል ኮማንደር ግርማ ያስረዱት። በዚሁ መሰረት ነገ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከደቡብ ፖሊስ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል። በአዲስ አበባ እና በባህርዳር በነበረው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት የተራዘሙ ሌሎች ቀሪ ሶስት የ28 ሳምንት ጨዋታዎች ነገ ይካሄዳሉ። በዚሁ መሰረት በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማ ከፐርሚየር ሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ እና በሃዋሳ ስታዲየም ሲዳማ ቡና ከድሬዳዋ ከተማ በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ይጫወታሉ። በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 11 ሰአት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርሲቲ ጋር ይገጥማል። የፕሪሚየር ሊጉ 29ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሰኔ 26 ቀን 2011 ዓ.ም የመጨረሻው የ30 ሳምንት ጨዋታዎች ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚካሄዱ የኢትዮጵያ አግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫውን ለማንሳት እና ላለመውረድ የሚደረገው ፉክክር አጓጊ ሆኗል። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ፋሲል ከነማ በ52 ነጥብ ሲመራ፤ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ50፣ ሲዳማ ቡና በ49 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። መከላከያ፣ ደቡብ ፖሊስ እና ቀድሞ ወደከፍተኛ ሊግ መውረዱን ያረጋገጠው ደደቢት ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ። ሀዲያ ሆሳዕና፣ ወልቂጤ ከተማ እና ሰበታ ከተማ በከፍተኛ ሊግ ውድድር ከየምድባቸው አንደኛ በመውጣት በ2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መሳተፋቸውን ያረጋገጡ ሲሆን ከፕሪሚየር ሊጉ የሚወርዱ ቀሪ ሁለት ክለቦች በቀሩት ሶስት ጨዋታዎች የሚለዩ ይሆናል። በፕሪሚየር ሊጉ በ35 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ወላይታ ድቻን ጨምሮ ስድስት ክለቦች የመውረድ ስጋት አለባቸው። የፕሪሚየር ሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የመቐለ ሰብዓ እንደርታው አማኑኤል ገብረሚካኤል እና የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በተመሳሳይ 15 ግቦች ሲመሩ የፋሲል ከነማው ሙጂብ ቃሲም በ14 ግቦች ይከተላል።