የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ከነገ በስቲያ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ከነገ በስቲያ ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ ሰኔ 21/2011 የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከነገ በስቲያ ይካሄዳሉ። እሁድ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት በፕሪሚየር ሊጉ ሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው መቐለ ሰብዓ እንደርታ በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ያስተናግዳል። በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ፌዴራል ፖሊስ ከመከላከያ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በሊጉ የ19ኛ ሳምንት መርሃ ግብር እሁድ ጎንደር ላይ ጎንደር ከተማ ከፕሪሚየር ሊጉ መሪ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ጋር ጨዋታቸውን ማድረግ ነበረባቸው። በአማራ ክልል አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት የክልሉ የስፖርት ኮሚሽን ጨዋታውን ለማካሄድ የሚያስችል ባለመሆኑ ጨዋታው እንዲራዘም ለኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ባቀረበው ጥያቄ መሰረት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ወደ ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም መዘዋወሩን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል። በ19ኛው ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ መርሃ ግብር ቡታጅራ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ጨዋታቸውን ማድረግ ነበረባቸው። ድሬዳዋ ከተማ በፋይናንስ ችግር ቡታጅራ ከተማ በጨዋታዎች ላይ በተደጋጋሚ ባለመገኘት የፎርፌ ውጤት እየተሰጠበት በመሆኑ ምክንያት ከውድድሩ ውጪ እንዲሆን መወሰኑ የሚታወቅ ሲሆን በዚሁ ምክንያት ጨዋታው አይካሄድም። ድሬዳዋ ከተማ እና ቡታጅራ ከተማ ከፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ውጪ በመሆናቸው የተሳታፊዎች ቁጥር ወደ ስምንት ዝቅ ብሏል። በተያያዘ ዜና በ15ኛ ሳምንት የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በተለያዩ ምክንያቶች ያልተካሄደው የከምባታ ዱራሜና የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ጨዋታ ነገ ዱራሜ ላይ ከረፋዱ አምስት ሰዓት ላይ እንደሚካሄድም ፌዴሬሽኑ ገልጿል። የፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በተመሳሳይ 30 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ይዘዋል። መቐለ ሰብዓእንደርታ በ24 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግን ዋንጫ ለማንሳት በሚደረገው ፉክክር ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከጎንደር ከተማ የሚጫወት ሲሆን ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከመቐለ ሰብዓ እንደርታና ከከምባታ ዱራሜ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል። ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ያሉትን ቀሪ ሁለት ጨዋታዎችን ካሸነፈ የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሲሆን ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሊጉ አሸናፊ ለመሆን የቀረውን አንድ ጨዋታ ማሸነፍና የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማን መሸነፍ ይጠብቃል። የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ሐምሌ 7 ቀን 2011 ዓ.ም ፍጻሜውን ያገኛል።