ቀጥታ፡

አየር መንገዱ ኮሊንስ ኤሮስፔስ ከተሰኘው የአሜሪካ ኩባንያ ጋር የ500 ሚሊዮን ዶላር የትብብር ስምምነት ተፈራረመ

ሰኔ 20 /2011የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአቪዬሽን፣ የህዋ እና የመከላከያ መሳሪያዎች አምራች ከሆነውና 'ኮሊንስ ኤሮስፔስ' ከተሰኘው የአሜሪካ ኩባንያ ጋር የ500 ሚሊዮን ዶላር የትብብር ስምምነት ተፈራረመ። በስምምነቱ መሰረት ኩባንያው ለመጪዎቹ 25 ዓመታት የማሞቂያና ማቀዥቀዣ፣ በአውሮፕላን ውስጥ የበረራ ደህንነት እንዲጠበቅ የሚያደርጉ በኤሌትሪክ፣ በውሃ ወይም በአየር ግፊት የሚሰሩ መሳሪያዎችን ጥገና አገልግሎት ይሰጣል። ከዚህም ሌላ ቦምባርዲየር በሚሰኘው የካናዳ አቪዬሽን ኩባንያ  የተመረቱና አየር መንገዱ የሚጠቀምባቸው 'ዲ ሃቪላንድ ካናዳ ዳሽ 8 ተርቦፕሮፕ ኪው - 400'  አውሮፕላኖች ጥገናም የስምምነቱ አካል መሆኑም ተመልክቷል። በመሆኑም ስምምነቱ አየር መንገዱ ይህንን የካናዳ ምርት አውሮፕላን  የሚጠቀሙ ሌሎች የአፍሪካ አገራት አየር መንገዶችን የጥገና ፍላጎት ለማሟላት እንደሚያስችለው የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ተናግረዋል። የአየር መንገዱ የስትራቴጂ ፍኖተ ካርታ በሆነው በራዕይ 2025 የተቋሙ የጥገና፣ እድሳት እና ምርምራ የስራ ክፍል በአፍሪካ ቀዳሚ አገልግሎት ሰጪ በመሆን የ600 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል። የአሜሪካው ኮሊንስ ኤሮስፔስ በዓለማችን በከፍተኛ ብዛት የአቪዬሽን፣ የህዋ እና የመከላከያ መሳሪያዎች አቅራቢ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነና መቀመጫውን በፍሎሪዳ ግዛት በምትገኘው "ዌስት ፓልም ቢች" ከተማ  ያደረገ ኩባንያ ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጥገና፣ እድሳት እና ምርምራ የስራ ክፍል ባለፈው 10 ዓመት ከፍተኛ የሚባል እድገት ያሳየና በተለያዩ ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች የጥገና አገልግሎቶችን እየሰጠ እንደሚገኝ አየር መንገዱ ገልጿል። ኤር ባስ፣ ቦይንግ እና ቦምባርዲየር አየር መንገዱ የጥገና አገልግሎት ከሚሰጣቸው አውሮፕላኖች መካከል ይጠቀሳሉ። በተጨማሪም የአየር መንገዱ የጥገና፣ እድሳት እና ምርምራ የስራ ክፍል በአፍሪካ ከሚገኙ ተመሳሳይ የስራ ክፍሎች በመቅደም የአሜሪካው የአቪዬሽን እቃዎች አቅራቢ በሆነው ጂኢ አቪዬሽን የሚመረቱ ጂኢኤንኤክስ ሞተሮችን ለማደስ የሚያስችል አቅም ያዳበረ እንደሆነም አየር መንገዱ ለኢዜአ በላከው መግለጫው አመልክቷል። የስራ ክፍሉ በሌሎች ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችም በተመሳሳይ በኢኒጅንና ለሃይል አቅርቦት የሚውሉ መሳሪያዎች ላይም እድሳት የማድረግ አቅም ማደበሩም ተገልጿል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2010 ዓ.ም በጀት ዓመት ብቻ ከአውሮፕላን ጥገና አገልግሎት ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ አግኝቷል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም