ቀጥታ፡

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል 40 የግል ጤና ተቋማት ላይ እርምጃ ተወሰደ--- የክልሉ ጤና ቢሮ

ሰኔ 20/2011 ህገወጥ ተግባራት ሲያከናውኑ ደርሼባቸዋለሁ ባላቸው 40 የግል ጤና ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ። በቢሮው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዋጮ ዋቡልጮ ለኢዜአ እንደገለጹት እርምጃው የተወሰደው ቢሮው ህገወጥ የምግብና የመድኃኒት ዝውውርን ለማስቆም አሰልጥኖ ባሰማራቸው የባለሙያዎች ቡድን አማካኝነት ነው። ከመጋቢት እስከ ሚያዝያ 2011 ዓ.ም በአሶሳና መተከል ዞኖች ሰባት ወረዳዎችና በአሶሳ  ከተማ አስተዳደር በተካሄደ የቁጥጥር ሥራ እርምጃው መወሰዱን ተናግረዋል። ከተቋማቱ መካከል ምንጫቸው ያልታወቀ መድኃኒቶችንና በመንግስት ተቋማት ብቻ መሸጥ የነበረባቸውን የወባ መድኃኒቶች እንዲሁም የኤች አይ ቪ ኤድስ መመርመሪያ መሳሪያ ለሽያጭ አቅርበው በመገኘታቸው እርምጃ የተወሰደባቸው መኖራቸውን ተናግረዋል። ከተሰጣቸው ፈቃድ ውጪ በግቢያቸው መድኃኒት ሲሸጡ የተገኙ ክሊኒኮችና ህመምተኞችን አስተኝተው ሲያክሙ የተደረሰባቸው የመድኃኒት መደብሮችም እርምጃው የተወሰደባቸው  መሆኑን አቶ ዋጮ ጠቅሰዋል ። “ደረጃቸውን ባልጠበቁ ሕንጻዎችና ያለሙያ ምዝገባ ፈቃድ አገልግሎት ሲሰጡ በነበሩ ተቋማት ላይም እርምጃው ተወስዷል “ ብለዋል ። በእዚህም አምስት የጤና ተቋማት ክስ ተመስርቶባቸው የመድኃኒት ምንጫቸውን ለፍርድ ቤት እንዳስረዱና እስከ ስድስት ወር የሚደርስ እገዳ የተጣለባቸው መሆኑን ተናግረዋል። ከእነዚህ በተጨማሪ ሁለት ተቋማት ፈቃዳቸው ሲሰረዝ 19ኝ የጤና ተቋማት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል ። ሌሎች 14ት ተቋማትም አገልግሎታቸውን እንዲያሻሽሉ ቀላል ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው  ነው ዳይሬክተሩ ያስታወቁት። በአሶሳ ከተማ ወረዳ 2 የመድኃኒት መደብርና መካከለኛ ክሊኒክ ባለቤት አቶ ለማ ብርሃኑ በበኩላቸው “ቢሮው በግል ጤና ተቋማት ላይ እያደረገ ያለውን ቁጥጥር በመንግስት ተቋማት  ላይም ሊያደርግ ይገባል” ብለዋል ።   በቂ የህሙማን ማስተናገጃ መቀመጫ እንኳ ሳይኖራቸው አገልግሎት የሚሰጡ የመንግስት የጤ ተቋማት መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ለማ ከመንግስት ጤና ተቋማት መድኃኒት ሰርቀው ለግሉ ዘርፍ የሚያቀብሉ ስነ-ምግባር የጎደላቸው ግለሰቦች ላይም ቁጥጥር ሊደረግ እንደሚገባ አመላክተዋል ።   የግል ጤና ተቋማት አገልግሎታቸው የተሟላ ነው ለማለት እንደማያስደፍር ሁሉ የ24 ሰዓት ፈቃድ ወስደው ተግባራዊ የማያደርጉ የጤና ተቋማት በመኖራቸው ቁጥጥሩ ሊጠናከር አንደሚገባ አቶ ለማ አስታውቀዋል።   በክልሉ 100 የሚጠጉ የግል ክልኒኮችና የመድኃኒት መሸጫ መደብሮች እንዳሉ መረጃዎችን ዋቢ አድርጎ የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም