የተደራቢ አውቶብሶችን የአገልግሎት ፍጥነት ለማሻሻል እየተሰራ ነው-የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
የተደራቢ አውቶብሶችን የአገልግሎት ፍጥነት ለማሻሻል እየተሰራ ነው-የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን
አዲስ አበባ ሰኔ 2/2010 የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን የተደራቢ አውቶብሶችን አገልግሎት ፍጥነት ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን አስታወቀ። ከአዲስ አበባ የትራንስፖርት በለስልጣን የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው በከተማዋ በቀን በአማካይ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን የጉዞ ምልልስ ፍላጎቶች አሉ። በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የጉዞ ፍላጎት ለማሟላት ከዚህ በፊት ከነበሩ የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭ አውቶብሶች በተጨማሪ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተደራቢ አውቶቡሶች አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ነው። ተደራቢ አውቶቡሶቹ ረዘም ላሉ የጉዞ መስመሮች አገልግሎት እየሰጡ ቢሆንም አልፎ አልፎ ተደራቢ አውቶብሶቹ ባዷቸውን ቆመው ህብረተሰቡ ታክሲዎችን በመጠበቅ ተሰልፎ ጊዜውን ሲያባክን ይስተዋላል። የብዙሃን ትራንስፖርት ተጠቃሚ የሆኑት አቶ ታደሰ ሹመት "ተደራቢ አውቶቡሶች ፍጥነት የላቸውም" ብለው ስለሚያስቡ እንደማይጠቀሙባቸው ይናገራሉ። በየጊዜው በከተማዋ የሚደርሱ የተሽከርካሪ አደጋዎች ፍርሃትም ተደራቢ አውቶብስን አማራጭ አድርጎ ላለመጠቀም ምክንያት መሆኑን አቶ ታደሰ ይገልፃሉ። የሸገር ብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት የኮሙኒኬሽን ደጋፊ የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ሳሙኤል ፍሰሃ አገልግሎት ላይ ካሉ 374 የሸገር አውቶቡሶች መካከል 25ቱ ተደራቢ መሆናቸውን ተናግዋል። የተደራቢ አውቶቡሶችን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻልም እየተሰራ ነው ይላሉ አቶ ሳሙኤል። አንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅትም አገልግሎት እየሰጡ ከሚገኙት 430 አውቶቡሶች መካከል 24ቱ ተደራቢ መሆናቸውን የድርጅቱ የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት አስተባባሪ አቶ ፍሬው ሰማ ለኢዜአ ተናግረዋል። የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ምትኩ አስማረ በበኩላቸው "ህብረተሰቡ ተደራቢ አውቶብሶችን ተመራጭ ያላደረገበትን ምክንያት ለይተን ለመፍተሄው እየሰራን ነው" ብለዋል። እነዚህን የህብረተሰቡን ጥያቄዎችን ለማሟላት ተደራቢ የብዙሃን አውቶብሶቹ መቀመጫ እንዲኖራቸው በማድረግና አውቶቡሶቹ ብቻ የሚጓዙበት መስመር በማዘጋጀት እየተሰራ መሆኑን ነው ዋና ስራ አስኪያጁ የገለጹት። በአዲስ አበባ የትራንስፖርት ፈላጊዎችና የአቅርቦት መጠን ባለመጣጣሙ በየቀኑ ከ2 ሚሊዮን በላይ የጉዞ ፍላጎቶች ሳይሰተናገዱ እንደሚቀሩ ከከተማው ትራንስፖርት ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ።