ቀጥታ፡

የችግኝ ተከላ ስራን በዘመቻ ብቻ ከማከናወን ዘላቂ ሥራ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ

ሰኔ 20/2011 የችግኝ ተከላ ስራ በዘመቻ ብቻ የሚከናወን ተደርጎ የሚወሰድ ቢሆንም  ከቅርብ ግዜ ወዲህ ዘላቂ ሥራ ሆኖ እንዲቀጥል እየተደረገ መሆኑን  የጉለሌ ክፍለ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ጽህፈት ቤት  ገልጿል። በዚህም አንድ ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በአካባቢ ጥበቃ እየለማ በመሆኑ ውጤት እያስገኘ ነው ተብሏል። የጉለሌ ክፍለ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ ጽህፈት ቤት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ቁጥጥር ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ወንደሰን ሽፈራሁ እንደተናገሩት የችግኝ ተከላ ስራን በዘመቻ ብቻ ከማከናወን በበጋ ወቅትም ዘላቂ ተግባር እየሆነ ነው። ክፍለ ከተማው ለችግኝ ተከላ የሚሄደውን ተቋምም ሆነ ማንኛውም አካል ክረምት ችግኝ ተክሎ እንዲሄድ አንፈቅድም ያሉት አቶ ወንደወሰን፤የችግኝ መትከያ ቦታ የምሰጡት በበጋ ወራትም ለተከሏቸው ችግኞች  በቂ እንክብካቤ ለማድረግ ሲስማሙ ብቻ እንደሆነ ነው ያብራሩት፡፡ በክፍለ ከማው ባለፉት አምስት ዓመታት አንድ ሺህ የሚጠጋ ሄክታር በአካባቢ ጥበቃ ሥራ እየለማ መሆኑንም ገልጸው፤ በዚህ ግዜ ከተተከሉ ችግኞች 83 በመቶ መጽደቁንም ተናግረዋል፡፡ በተለይ ተቋማት ለችግኝ ተከላ የተሰጣቸውን ቦታ በበጋ ወራትም ውሃ የሚያጠጡበትና እንክብካቤ የሚያደርጉበት አሰራር በመዘርጋቱ ሥራው ባህል እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል። በክፍለ ከተማው በሚገኙ ጥብቅ ደኖች ላይ የተተከሉ ችግኞች ክትትል እየተደረገባቸው ነው ያሉት አቶ ወደወሰን፤ የተተከለ ችግኝ ቀጣይነት ባለው መልኩ እንክብካቤ ካልተደረገለት ዋጋ እንደማይኖረው ነው ያብራሩት፡፡ በአሁኑ ወቅት ችግኝ ለሚተክሉ ተቋማት የቁሳቁስ ድጋፍ በመስጠትና ግንዛቤ የመፍጠር ስራ በማከናወን በከተማዋ ከሚገኙ ክፍለ ከተሞች ና ከፌዴራል ተቋማትም ሞዴል ለመሆን የበቁ መኖራቸውን ጠቅሰዋል። በየአመቱ የሚተከሉ ችግኞች ከእንስሳና ከሰው ንክኪ እንዲጠበቁ አንድ መቶ ያህል የጥበቃ ባለሙዎች መሰማራታቸውንም  አብራርተዋል፡፡ ፖስታ አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት፣ የግል ድርጅቶች ሰራተኛና ማህበራዊ ዋስት ኤጅንሲ ና ሌሎች ውስን ተቋማት በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ አርአያ  መሆናቸውን ነው አስተባባሪው  ያስረዱት። በክፍለ ከተማው በዚህ አመት 120 ሺህ ችግኞችን በጥብቅ የደን ቦታ፤ 30 ሺህ ያህሉን ደግሞ  በመኖሪያ አካባቢዎች ለመትከል ዝግጅት መደረጉም ተገልጿል። የግል ድርጅቶች ሰራተኛና ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ የአካባቢ እንክብካቤና ጥበቃ ማስተባበሪያ ሰብሳቢ አቶ ቅዱስ ሀጎስ በበኩላቸው ኤጀንሲው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ  ለችግኝ ተከላ ና እንክብካቤ ትኩረት ሰትቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በእቅዱ ውስጥ የአካባቢ ጥበቃ ስራን በዋናው መስሪያ ቤት ና 11ዱን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶቹን በማካተት በየወሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት፤ በዓመት ሁለቴ የተከሏቸውን ችግኞች  ውሃ በማጠጣትና  በመኮትኮት እንደሚንከባከቡ  ነው የገለጹት። ከዚህ በተጨማሪ የኤጄንሲው ሰራተኛ ለአካባቢ ጥበቃ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ የጉብኝት ፕሮግራም በማዘጋጀት ሞዴል የሆኑ አካባቢዎችን እንዲጎበኙ በማድረግና በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ ግንዛቤ እንዲያገኙ በባለሙያ ማብራሪያ እንዲሰጥ መደረጉንም አብራርተዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም