በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን የፀረ-አበረታች መድሀኒት ፎረም ተመሰረተ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን የፀረ-አበረታች መድሀኒት ፎረም ተመሰረተ
ሰኔ 20/2011 ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገሮች የመጀመሪያ ነው የተባለውን የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የፀረ-አበረታች መድሀኒት ፎረም መሰረተች። የፎረሙ ዓላማ በኢትዮጵያና ዓለም አቀፍ ደረጃ ለስፖርቱ ፈተና እየሆነ የመጣውን የአበረታች መድሃኒቶች መጠቀም ስጋት ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ነው። ኢትዮትጵያ በ2009 ዓ.ም ብሄራዊ ፀረ-አበረታች መድሃኒቶች ጽህፈት ቤት መስርታ ችግሩን የመከላከል ሥራ መጀመሯ ይታወቃል። የአትሌቶች አበረታች መድሀኒት ምርመራ፣ የፀረ- አበረታች መድሃኒት አጠቃቀም ግንዛቤ ፈጠራና ችግሩን ለመቆጣጠር የሚያግዙ የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀት እስካሁን እየተከናወኑ ካሉት የፅህፈት ቤቱ ተግባራት መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ፅህፈት ቤቱ ለአበረታች መድሃኒት አጠቃቀም የበለጠ ተጋላጭ ናቸው ብሎ በለያቸው በአትሌቲክስ፣ በእግር ኳስ፣ በብስክሌት፣ በፓራኦሎምፒክና ቦክስ ስፖርቶች ላይ የቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑም ተመልክቷል። የመገናኛ ብዙሃን ፎረሙ በይፋ በተመሰረተበት ስነ-ስርዓት ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ አበረታች መድሃኒቶች ጽህፈት ቤት የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር አክሊሉ አዛዥ ተገኝተዋል። በዚሁ ወቅት ፕሮፌሰር አክሊሉ እንዳሉት ኢትዮጵያ አበረታች መድሀኒትን ለመከላከል ባሳየችው ቁርጠኝነትና በተከናወኑት ተግባራት በአፍሪካ ደረጃ ችግሩን በመከላከል ረገድ የሚበረታታ ስራ እየከወኑ ካሉ ግንባር ቀደም ሀገሮች መካከል አንዷ እንድትሆን አስችሏታል። ጋዜጠኞችን ያቀፈው ፎረሙ መመሰርቱም አገሪቱ ችግሩን የመከላከል ተግባሯን የበለጠ አጠናክራ ለመቀጠልና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችም በዚህ ረገድ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በመወጣት የፅህፈት ቤቱን ተግባር ለማገዝ ያስችላል ብለዋል።ሠ ፎረሙ በተለይም በቀላሉ ወደ ህብረሰተቡ ተደራሽ ለመሆንና በችግሩ ዙሪያ ሰፊ ግንዛቤን በመፍጠር አበረታች የመድሀኒት መድሃኒት አጠቃቀም ችግርን ለመካላከል የላቀ አስተዋጽኦ ይኖረዋለ ሲሉም ገልፀዋል።