ቀጥታ፡

የህዝቦች የጋራ እሴት ኢትዮጵያ ላይ የተጋረጠው ፈተና አሁን ካለው የከፋ እንዳይሆን ማድረጉ ተገለጸ

ሰኔ 20/2011የህዝቦች የጋራ እሴት ኢትዮጵያ ላይ የተጋረጠው ፈተና አሁን ካለው የከፋ እንዳይሆን ማድረጉን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ። ኢትዮጵያውያን የውጭ ጠላትን በጋራ ከመመከት ባለፈ በሌሎች አገሮች ላይ እንደሚያጋጥመው የሃይማኖት እና ሌሎች  ግጭቶች ስጋት የሌለባቸው ሰላማዊ ህዝቦች እንደሆኑም አንስተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተመሳሳይ ብሄሮችና ተመሳሳይ እምነት ተከታዮች ጭምር መስማማት አቅቷቸው አላስፈላጊ ቁርሾና ግጭት ውስጥ እየገቡ የአገሪቷ ሰላም እየተናጋ መሆኑን ባለሙያዎቹ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ህዝቦች ለረጅም ዓመታት የገነቡት የመተባበር የመከባበርና ችግሮችን በብልሃት የመፍታትና የማለፍ እሴት ባለቤቶች እንደሆኑም ገልጸዋል። በህዝቦች መካከል  ቀደም ሲል የተገነባ ጠንካራ የመቻቻልና የመከባበር እሴት ባይኖር ኖሮ አገሪቷ በአሁን ጊዜ እየታየ ባለው ሁኔታ ከዚህ የከፋ አደጋ ይጋረጥባት እንደነበርም ነው ያነሱት። ምሁራኑም  ይህ ችግር በጊዜ ካልተፈታ የአገሪቷን ውስጣዊ ሰላም ከማናጋት ባለፈ ጀግኖች አባቶች በታላቅ መስዕዋትነት ያቆዩትን አገር በማፈራረስ የታሪክ ተወቃሽ የሚያደርግ ነው ብለዋል። ከጥንት ጀምሮ በጋራ በኖሩ ህዝቦች መካከል መለያየትና ጥላቻ እንደሌለና አሁን እየታየ ያለው መለያየትና ጥላቻ የራሳቸውን ጥቅም በሚያስቀድሙ አካላት የተቀነባበረ መሆኑን ባለሙያዎቹ ይናገራሉ። በአሁን ጊዜ አገሪቷ የተጋረጠባትን አደጋ ሁሉም አካል የየራሱን ድርሻ በአግባቡ በመወጣት ወደ ቀደመ ገናናነቷ መመለስ እንዳለበትም ነው ባለሙያዎቹ የሚገልጹት።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም