የኢትዮጵያ የክብደት ማንሳት ሻምፒዮና ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የክብደት ማንሳት ሻምፒዮና ተጀመረ

አዲስ አበባ ሰኔ 20/2011 15ኛው የኢትዮጵያ የክብደት ማንሳት ሻምፒዮና ትናንት በአዲስ አበባ ጃን ሜዳ ተጀምሯል:: በሻምፒዮናው ላይ የትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ የሐረሪ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች እንዲሁም የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ። በወንድ 40 በሴት 25 በድምሩ 65 ተወዳዳሪዎች ተሳታፊ ሲሆኑ በወንዶች ከ55 እስከ 102 ኪሎ ግራም በሴቶች ከ45 እስከ 71 ኪሎ ግራም ውድድሮቹ የሚሳተፉባቸው የክብደት ዘርፎች ናቸው። የኢትዮጵያ ክብደት ማንሳት እና ሰውነት መገንባት ፌዴሬሽን የጽህፈት ሃላፊ አቶ አበበ አሽኔ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሻምፒዮናው አላማ በነሐሴ ወር 2011 ዓ.ም በሞሮኮ ርዕሰ መዲና ራባት በሚካሄደው 12ኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታ የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎችን ለመምረጥ ነው። በሁለቱም ጾታዎች በሻምፒዮናው ጥሩ ተፎካካሪ የሆኑና በአፍሪካ ከሚገኙ ተወዳዳሪዎች ተቀራራቢ ውጤት ያስመዘገቡ ተወዳዳሪዎች ለመላው አፍሪካ ጨዋታ እንደሚመረጡም ተናግረዋል። የአማራ፣ ሶማሌ፣ አፋር እና ጋምቤላ ክልሎች በበጀት እጥረት እና በዝግጅት ማነስ በሻምፒዮናው ላይ እንደማይሳተፉ መግለጻቸውን አመልክተዋል። ትናንት ሻምፒዮናው ሲጀመር ሶስት የፍጻሜ ውድድሮች ተካሄደዋል። በ55 ኪሎ ግራም ወንዶች የትግራይ ክልል ተወዳዳሪ የሆነው ተክለብርሃን ኤፍሬም የወርቅ ሜዳሊያ ሲያገኝ አበባው ገደፋው ከኦሮሚያ ክልል ሙሴ ተክለ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል የብርና የነሐስ ሜዳሊያ አግኝተዋል። በ61 ኪሎ ግራም ወንዶች የቤኒሸንጉል ጉምዙ ተወዳዳሪ ሀብታሙ ጴጥሮስ አሸናፊ የኦሮሚያ ክልሉ ኤርሚያስ ዘውዴ ሁለተኛ ወጥቷል። በ61 ኪሎ ግራም ወንዶች ለመወዳዳር ሰባት ተወዳዳሪዎች ቢመዘገቡም አምስቱ ተወዳዳሪዎች ከክብደት በላይ በመሆናቸው ከውድድሩ ውጪ ሆነዋል። በዚሁ መሰረት በክብደት ዘርፉ ሁለት ተወዳዳሪዎች ብቻ በመሳተፋቸው በክብደት ማንሳት ውድድር ህግ መሰረት በፍጻሜ ውድድር ላይ ከሶስት በታች ተወዳዳሪ የሚሳተፍ ከሆነ አንደኛና ሁለተኛ የሚወጡ ተወዳዳሪዎች የሜዳሊያ ተሻላሚ አይሆኑም። በዚሁ መሰረት ሀብታሙ ጴጥሮስ እና ኤርሚያስ ዘውዴ አንደኛና ሁለተኛ ቢወጡም የሜዳሊያ ሽልማት አያገኙም። በሴቶች 45 ኪሎ ግራም የኦሮሚያ ክልል ተወዳደሪ የሆነችው ፀጋዓለም አስፋው የወርቅ ሜዳሊያ ስታገኝ ህይወት ተስፋዬ ከትግራይ ክልል ኑሀሚን ጸጋዬ ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል። በሻምፒዮናው የዛሬ የሁለተኛ ቀን ውሎ በወንዶች 67 እና 73 ኪሎ ግራም እንዲሁም በሴቶች በ49 እና 55 ኪሎ ግራም የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳል ተብሎ መርሃ ግብር ቢያዝም ከባድ ዝናብ በመጣሉ የተነሳ ለነገ እንዲተላለፉ መደረጉ ታውቋል። 15ኛው የኢትዮጵያ የክብደት ማንሳት ሻምፒዮና እስከ ሰኔ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ይቆያል። በሰኔ ወር 2010 ዓ.ም በሐረሪ ክልል በተካሄደው 14ኛው የኢትዮጵያ የክብደት ማንሳት ሻምፒዮና በወንዶች የትግራይ ክልል በሴቶች የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል። በሌላ በኩል አራተኛው ዙር የብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ሻምፒዮናው በቀጣዩ ሳምንት በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ይካሄዳል። ከሰኔ 26 እስከ 29 ቀን 2011 ዓ.ም በሚካሄደው ውድድር ከ8 እስከ 10 ክለቦች የተወጣጡ 70 ተወዳዳሪዎች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል። በወንዶች ከ49 እስከ 91 ኪሎ ግራም በሴቶች ከ48 እስከ 60 ኪሎ ግራም ውድድር የሚካሄድባቸው የክብደት ዘርፎች ናቸው። የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የውድድርና የስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የውድድሩ አላማ በነሐሴ ወር 2011 ዓ.ም በሞሮኮ ርዕሰ መዲና ራባት በሚካሄደው 12ኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታ የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎችን ለመምረጥ ነው። በዚሁ መሰረት እስካሁን በድሬዳዋ፣ በወላይታ ሶዶና ደሴ ከተሞች በተካሄዱት ውድድሮች ውጤታቸውን መሰረት በማድረግ ዘጠኝ ወንድ ሁለት ሴት በድምሩ 11 ስፖርተኞችን ለመላው አፍሪካ ጨዋታ መምረጥ መቻሉን ተናግረዋል። የተመረጡት ስፖርተኞች ከግንቦት ወር 2011 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ስልጠና እየወሰዱ እንደሆነና በአዲስ አበባ በሚካሄደው ውድድር ተጨማሪ ስፖርተኞች ተመርጠው ቀድመው ከተመረጡት ጋር ወደ ስልጠና እንደሚገቡም አመልክተዋል። የኢዜአ ሪፖርተር ከተመረጡት ስፖርተኞች መካከል የሴቶች ቁጥር ለምን አነሰ? በሚል ላነሳው ጥያቄ በውድድሮቹ ላይ የሚሳተፉ ክለቦች የሚያሳትፏቸው ሴት ተወዳዳሪዎች ቁጥር ዝቅተኛ እንደሆነ አቶ ስንታየሁ ገልጸዋል። በአዲስ አበባ በሚካሄደው ውድድር ላይ የተሻለ ብቃት ያላቸው ሴት ተወዳዳሪዎች ተመርጠው በመላው አፍሪካ ጨዋታ በሚሳተፈው ብሔራዊ ቡድን ውስጥ እንደሚካተቱም ገልጸዋል። ለክለቦች የውድድር አማራጮችን ከማስፋት አንጻርም የውድድሩ መካሄድ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አቶ ስንታየሁ አብራርተዋል። በአራት ዙር በሚካሄዱት ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር ያሉ ውጤቶች ተደምረው በሁለቱም ጾታዎች አጠቃላይ አሸናፊ እንደሚለይም ተናግረዋል። በሚያዚያ ወር 2011 ዓ.ም በደሴ ከተማ በተካሄደው ሶስተኛ የብሔራዊ የክለቦች የቦክስ ሻምፒዮና በወንዶች ማራቶን፣ በሴቶች አዲስ አበባ ፖሊስ ክለቦች አሸናፊ መሆናቸው የሚታወስ ነው።