ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከ'ለሁሉ የክፍያ ማዕከል' ጋር የነበረውን የአገልግሎት ውል ስምምነት ሊያቋርጥ ነው

አዲስ አበባ ሰኔ 20/2011የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከ'ለሁሉ የክፍያ ማዕከል' ጋር የነበረውን የአገልግሎት ውል ስምምነት ሊያቋርጥ መሆኑን አስታወቀ። አገልግሎቱ ዛሬ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ በአሁን ወቅት ተቋሙ ለደንበኞቹ የሚሠጠውን አገልግሎት ለማቀላጠፍና ወርሃዊ የኃይል ፍጆታ ክፍያ ሥርዓትን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ ዝግጅቱን አጠናቋል። በመሆኑም በ'ለሁሉ የክፍያ ማዕከል' ሲፈፀም የነበረውን የክፍያ ስርዓት ከሰኔ 26 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ይቋረጣል። ለአፈፃፀሙ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የስምምነት ሰነድ የተፈረመ መሆኑን የገለጸው አገልግሎቱ፤ የከፍተኛና መካከለኛ ኃይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች፣ የንግድ እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ክፍያቸውን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መፈፀም የሚችሉ መሆኑን አመልክቷል። ተቋማቱ በባንክ እንዲከፍሉ የተቀመጠው አሰራር የሚያስገድድ በመሆኑ በየአገልግሎት መስጫ ማዕካላት ተገኝተው የውል ስምምነት እንዲፈፅሙ ጥሪ ቀርቧል። ክፍያቸውን በባንክ ለመፈፀም ፍላጎቱ ያላቸው የመኖሪያ ቤት ደንበኞች በየአገልግሎት መስጫ ማዕከላት በመሄድ የውል ስምምነት እንዲፈፅሙ የጠየቀው አገልግሎቱ፤ ለጊዜው ክፍያቸውን በባንክ ለመክፍል ያልተዘጋጁ የመኖሪያ ቤት ደንበኞች በአቅራቢያቸው በሚገኝ በየትኛውም የአገልግሎት መስጫ ማዕከል ወርሃዊ የፍጆታ ሂሳብ መክፍል እንደሚችሉ ገልጿል። አብዛኛው የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት በኢንተርፕራይዝ ሪሶርስ ፕላኒንግ (በቴክኖሎጂ) የተሳሰሩ በመሆናቸው፤ ደንበኞች በመረጡት የአገልግሎት መስጫ ማዕከል በአካል በመሄድ የፍጆታ ሂሳባቸውን መክፈል የሚችሉ መሆኑን አገልግሎቱ አስታውቋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ወርሀዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ ክፍያን በአዲስ አበባ፣ በባህርዳር እና በመቐለ ከተሞች በሚገኙ በ40 የለሁሉ የክፍያ ማዕከላት ሲያከናውን መቆየቱ ይታወቃል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም