በነቀምቴ የችግኝ ተከላና የደም ልገሳ ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
በነቀምቴ የችግኝ ተከላና የደም ልገሳ ተካሄደ
ነቀምቴ ሰኔ 20 / 2011 በነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች የችግኝ ተከላና የደም ልገሳ አካሄዱ። የችግኝ ተከላና የደም ልገሳውን ያካሄዱት የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣የኦሮሚያ ህብረት ስራና የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንኮች ሠራተኞች ናቸው። ነዋሪዎቹ ተከላውን ያካሄዱት በደርጌ ክፍለ ከተማ ለአረንጓዴ ልማት ተብሎ በተከለለ መሬት ላይ ነው ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ከርስቲያንን የወከሉት ቄስ መላከፀሐይ በሪሁን የከተማው አስተዳደር ባወጣው መርሐ ግብር መሰረት የሃይማኖት አባቶች በተከላው መሳተፋቸውን ገልጸዋል። “ችግኝ መትከል ብቻውን ትርጉም ያለው ባለመሆኑ በእንክብካቤውም እንሳተፋለን” ብለዋል ። “ችግኝ ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ በተከላው ተሳትፈናል” ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ማዕከላዊ ሲኖዶስ የክርስቲያን ማሰልጠኛ ኮሌጅ መምህር ቄስ አስፋው ተርፋሳ ናቸው። የነቀምቴ ከተማ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ረጋሳ ሞሲሳ በመርሐ ግብሩ ከአንድ ሚሊዮን ችግኞች እንደሚተከሉና እንዲጸድቁ እንክብካቤ ይደረግላቸዋል ብለዋል። መርሐ ግብሩ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚዘልቅም ገልጸዋል። ከመርሐ ግብሩ ጋር ተያይዞ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የነቀምቴ ዲስትሪክት ሠራተኞች በደም እጦት የሚቸገሩ ወገኖችን ለመርዳት ደም ለግሰዋል።