የመጨካከን መጥፎ የፖለቲካ ጉዞ ዋጋ አስከፍሏል--የፖለቲካ ልሂቃን - ኢዜአ አማርኛ
የመጨካከን መጥፎ የፖለቲካ ጉዞ ዋጋ አስከፍሏል--የፖለቲካ ልሂቃን
ሰኔ 20/2011 በኢትዮጵያ የመጨካከን መጥፎ የፖለቲካ ጉዞ ገፅታን ለመቀየር ሀቀኛ ድርድርና ብሔራዊ መግባባት እንደሚያስፈልግ የፖለቲካ ልሂቃን ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እንዳሉት፤ እንደሰሞኑ ያሉ የአመራር ግድያዎች በኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዞ ብዙ ጊዜ ታይተዋል። እንዲህ ዓይነት ክስተቶች የሚመጡት ከፖለቲካ ቡድኖች “ተገፍተናል፣ በቂ ስልጣን አላገኘንም ከሚል ፖለቲካዊ መሠረት እና በህዝቡ ውስጥ የመጠቃትና የመገፋት ስሜት ሲታይ ነው” ብለዋል። በአሁኑ ወቅት በፖለቲካ ሂደቱ ላይ ቅሬታ ያላቸው ኃይሎች መኖራቸውና ስሜቱ በህብረተሰቡ ውስጥም መስፋፋቱ አሳሳቢ እንደሆነ ነው ያብራሩት። የማህበረሰቡን የመገፋትና የመጠቃት ስሜት ለማርገብ የፖለቲካ ሃይሎች አንድነትና ልዩነታቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ያደረጉት ጥረት ግልፅ አለመሆኑንም ተችተዋል። ለውጡ እኛ በምንፈልገው ጥልቀትና ፍጥነት እየተጓዘ አይደለም በሚሉት እና መሃል ላይ ባሉት ሃይሎች መካካል አለመግባባት መኖሩ ጉዳት እያስከተለ መሆኑንም ነው ፕሮፌሰር መረራ ያነሱት። የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ በበኩላቸው፤ የሰሞኑ ግድያ “በውስጥ ጠላት” የተፈጸመ መሆኑ ተቀባይነት እንደሌለው አንስተው፤ እንደ ሀገር የተጀመረው የተስፋ ጉዞ ላይ ሳንካ ይፈጥራል ብለዋል። “በመካከላችን ያሉ ችግሮችን በተባበረ ክንድ ካላስወገድን ቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር ሊፋፋም ይችላል” ሲሉም ነው ስጋታቸውን የገለጹት። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክና ባህል ከቀዳማዊ አፄ ሃይለ ስላሴ እስከ ኢህአዴግ ጠብመንጃና ጉልበት የስልጣን ማስጠበቂያና መቀሚያ ሆነው እንደቆዩም ፕሮፌሰር መረራ ያስታውሳሉ። “በንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ የነበሩ ፖለቲካዊ ልዩነቶች በሃይል ለመፍታት ተሞክሯል፤ በኋላም ንጉሡን በማሰርና በመግደል በደም የተመራ ፖለቲካዊ ለውጥ ነው የነበረው፤ ኢህአዴግ ከጫካ ወደ አዲስ አበባ ከገባ በኋላም የኃይል እርምጃዎችን አላቆመም” ነው ያሉት። መደበኛ ወታደራዊና የደህንነት ስራው ጥያቄ ውስጥ ገብቷል ያሉት አቶ ተሻለ፤ ቁንጮ ላይ ያሉ ወታደራዊ መኮንኖች መገደላቸው በህብረተሰቡ የደህንነት ስጋት ፈጥሯል ብለዋል። ፖለቲከኞች ብሔራዊ መግባባትን ወደ ጎን ማለታቸው ዋጋ እያስከፈለ ነው ያሉት አቶ ተሻለ፤ ኢህአዴግም በአጀንዳው ዙሪያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዎንታዊ ምልሽ ቢያሳይም እየተገበረው እንዳልሆነ ይገልጻሉ። በአሁኑ ወቅት ከብሔረሰቦች ጥያቄ ጋር በተያያዘ የከረረ ፖለቲካ መኖሩን የሚናገሩት ፕሮፌሰር መረራ፤ የሰሞኑ የመገዳደል ሂደት በአጭሩ ባይገታ የሌሎችን ሀገራት አስፈሪ ሁኔታ ሊፈጥር ይችል ነበር ብለዋል። “ብዙ የፖለቲካ ኃይሎች መንግስትና የምርጫ ቦርድ በሚሰበስቡን ወቅት ተጯጩሆ ከማለፍ በስተቀር በአጀንዳዎች ላይ ውይይትና ክርክር እያደረግን አይደለም” ነው ያሉት። አቶ ተሻለ እንዳሉት “የዘመመውን ቤታችን ማቆም ካስፈለገ የገመድ ጉተታውን አጥብቀው የያዙ ሃይሎች፣ ህዝብና መንግስት ፈታኙን ጊዜ ለማለፍ በፅሞና ማሰብ አለባቸው”። የበቀልና የመጨካከን ፖለቲካ አክሳሪ ነው ያሉት አቶ ተሻለ፤ ጎጂ አካሄዶችን ለማስወገድ መንግስት ህጋዊ እርምጃዎችን በሰከነ ሁኔታ መውሰድ አለበት ብለዋል። ፕሮፌሰር መረራ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሂደቱ ፈተናዎች ላይ በሰከነ ሁኔታ በመደራደር ወደ ጋራ ጉዳዮች መምጣት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል። መንግስት በራሱ ሃይሎች መካከል ያለውን ገመድ ጉተታ በማቆም የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ቁርጠኛ እርምጃ እንዲወስድም ጠይቀዋል። የእርስ በእርስ መገዳደል እና መጎዳዳት ፖለቲካዊ ጉዞ ላለፉት 50 ዓመታት የኢትዮጵያን ህዝብ ዋጋ በማስከፈሉ ቆም ብሎ ማሰብ እንደሚገባም ፕሮፌሰር መረራ መክረዋል። የዴሞክራሲ ስርዓትን ለማጠናከር ብሔራዊ መግባባት እየተሰበከ ባለበት ወቅት በጸጥታና ደህንነት ሃይሎች እየታየ ያለው ክፈተት ችግር እየፈጠረ መሆኑን አቶ ተሻለ ተናግረዋል። “በ11ኛው ሰዓት ከመሯሯጥ አስቀድሞ ችግሮችን መፍታት ይገባል” ያሉት አቶ ተሻለ፤ ፖለቲከኞች በልዩነቶቻቸው ዙሪያ በመወያየትና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር፤ ስር ነቀል ፖለቲካዊና ህጋዊ እርምትን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።