ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኡጋንዳ ከፍተኛ ደረጃ ሜዳሊያ ተሸለሙ

ኡጋንዳ ሰኔ 2/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኡጋንዳ ከፍተኛ ደረጃ ሜዳሊያ ተሸለሙ። ሽልማቱ የተበረከተላቸው 29ኛው የኡጋንዳ የብሔራዊ ጀግኖች በዓል በዛሬው ዕለት በተከበረበት ወቅት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማቱን ከኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ እጅ ተቀብለዋል። ሽልማቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ በቀጣናውና በአፍሪካ ደረጃ ላከናወኑት ተግባርና አስተዋጽኦ ነው። ትናንት በአገሪቱ ብሔራዊ ቤተ መንግስት ታላቅ አቀባበል የተደረገላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ጋር በሁለትዮሽ፣ አህጉራዊና ዓለማቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል። መሪዎቹ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ከፍ የማድረግ አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኡጋንዳ ካምፓላ ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት ጋርም ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም