በምዕራብ ኦሮሚያ 'የኦነግ ሸኔ' በመባል የሚታወቀው ቡድን የሚፈጽመውን ድርጊት ነዋሪዎች አወገዙ - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ኦሮሚያ 'የኦነግ ሸኔ' በመባል የሚታወቀው ቡድን የሚፈጽመውን ድርጊት ነዋሪዎች አወገዙ
አዲስ አበባ ሰኔ 19/2011 በምዕራብ ኦሮሚያ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሸኔ በመባል የሚታወቀው ቡድን የሚፈጽመውን ድርጊት እንደሚያወግዙ ነዋሪዎች ባካሄዱት የተቃውሞ ሰልፍ ገለጹ። በምዕራብ ኦሮሚያ በተለያዩ ዞኖች በመንቀሳቀስ የህዝቡን ሰላምና መረጋጋት የሚያውከውን የኦነግ ሸኔ ቡድን ድርጊት በማውገዝ የተቃውሞ ሰልፍ ትናንት ተካሂዷል። የቄለም ወለጋ፣ የምዕራብና ምስራቅ ወለጋ እንዲሁም ቡሎ በደሌ የተለያዩ ወረዳዎች ነዋሪዎቹ ''የኦሮሞን ህዝብ ነጻ አወጣለሁ'' በማለት ጫካ የገባ ማንኛውም ቡድን እንደማይወክላቸው ትናንት ባካሄዱት የተቃውሞ ሰልፉ ላይ ባሰሙት መፈክርም አረጋግጠዋል። በተለያዩ ዞኖች በተካሄዱት በነዚህ የተቃውሞ ሰልፎች ለኦሮሞ ህዝብ ጥቅም የሚታገል በማስመሰል ዘረፋና ግድያ የሚፈጽመው የኦነግ ሸኔ ቡድን እንቅስቃሴን በመግታት መንግስት የህግ የበላይነትን እንዲያስጠብቅ የሰልፎቹ ተሳታፊ ወጣቶች ጠይቀዋል። የተቃውሞ ሰልፈኞቹ እንደገለጹት፤ “በኦሮሞን ህዝብ ስም ጫካ ገብቻለሁ” የሚለው ቡድን ማንንም አይወክልም። ይህን የሚፈጽሙ ሃይሎች የኦሮሞ ህዝብ ለረጅም ዓመታት ታግሎ ያገኘውን ድል ወደ ኋላ ለመቀልበስ የሚጥሩ ናቸው። በምዕራበ ኦሮሚያ በሚገኙ ዞኖች ፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ትናንት ባካሄዱት በዚሁ የተቃሞ ሰልፍ ቡድኑ ለወገን የሚሰራ በማስመሰል በህዝቡ ላይ ስቃይና መከራ እያደረሰ ነው። በኦነግ ሸኔ ስም ሰላምን ማወክና ህዝብን ማሸበርን አጥብቀው የሚቃወሙት ድርጊት እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተውታል። ኦነግ ባለፈው ወር በይፋ የትጥቅ ትግል እንደማያካሂድና ሰራዊትም እንደሌለው ማስታወቁ ይተወሳል። ትግሉ ሰላማዊ እንደሚሆን ይፋ አድርጓል። የኦሮሞን ህዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ ከሌሎች ጋር በሀሳብ ተወዳድሮ ለማሸነፍ መወሰኑን በስምምነት አረጋግጧል። ይህም ሆኖ ኦነግ ሸኔ የተባለው ቡድን በሰዎች ላይ ጥቃት እየፈጸመና ንብረት እያወደመ መሆኑን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል። የኦሮሞን ህዝብ ወክያለሁ በማለት ጫካ የሚገኘውን ቡድን ለመቃወም በተካሄደው በዚሁ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ነዋሪዎቹ “በኦሮሞ ህዝብ ስም ታጥቆ ጫካ የሚገኘው ኃይል አይወክለንም፣ በኦነግ ስም በመታጠቅ ሰላምን ማወክና ህዝቡን ማሸበርን እንቃወማለን” የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል። ኦነግ ከመንግስት ጋር እርቅ በማውረድ ወደ ሰላማዊ ትግል መግባቱን የገለጹት የተቃውሞ ሰልፈኞቹ ''በኦነግ ስም ታጥቆ ጫካ የሚገኘው ሽፍታ እውቅና የለውም'' በማለት ሲገልጹ በግል የደረሰባቸውንም በደል በመዘርዘር ነው። የተቃውሞ ሰልፈኞቹ አገሪቷን ወደ ዴሞክራሲያዊነት ለማሸጋገር ሁሉም ዜጋ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀው ሰልፈኞቹ ፤ በዚህ ዘመን የትጥቅ ትግል በማካሄድ ወደስልጣን ለመምጣት ማሰብ ተቀባይነት የሌለው ድርጊት መሆኑን ገልጸዋል። መንግስት የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥና ዴሞክራሲን ለማስፈንና የሚያደርገውን ጥረት ህዝቡ እንዲደግፍ ጠይቀዋል። ህብረተሰቡም የአካባቢውን ሰላም ነቅቶ በመጠበቅ በልማቱና በለውጡ ቀጣይነት ላይ የጀመረውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ተላልፏል።