አደንዛዥ እጾችን መጠቀምና መጤ ልማዳዊ ድርጊቶች በአገሪቱ እየተስፋፉ መምጣታቸው ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
አደንዛዥ እጾችን መጠቀምና መጤ ልማዳዊ ድርጊቶች በአገሪቱ እየተስፋፉ መምጣታቸው ተጠቆመ
ጋምቤላ ሰኔ 2/2010 አደንዛዥ እጾችን መጠቀምና መጤ ልማዳዊ ድርጊቶች በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች እየተስፋፉ መምጣታቸውን የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤና ቁጥጥር አስተዳደር ባለስልጣን ገለጸ። በአሉታዊ መጤ ልምዶችና በአደንዛዥ እጾች ላይ ያተኮረ የአንድ ቀን የምክክር መድረክ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል። የባለስልጣኑ ምክትል ዳሬክተር ዶክተር ኸይረዲን ረዲ በዚህ ወቅት እንዳሉት አደንዛዥ እፆችና መጤ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በተለይ በወጣቱ ትውልድ ላይ ተጽዕኖ እያደረሱ ነው። እንደ ምክትል ዳይሬክተሩ ገለጻ ቀደም ሲል በሀገሪቱ ሱስ አስያዥ አደንዛዥ እፆች፣ መድኃኒቶችና አሉታዊ መጤ ልምዶች ብዙ ያልተለመዱ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት እድሜና ሃይማኖት ሳይገድበው በሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች በስፋት እየተዘወተሩ ይገኛሉ። ሕብረተሰቡን የሚጎዱ አደንዛዥ እፆችን የመጠቀም ሁኔታና መጤ ልምዳዊ ድርጊቶች የመፈጸም አዝማሚያ በተለያዩ የአገሪቱ አካቢዎች በስፋት እየተስተዋለ መምጣቱንም አስታውቀዋል። ችግሩ በተለይ በትምህርት ተቋማት በስፋት የሚዘወተር መሆኑ ስዕብናው የተገነባ ሀገር ተረካቢና አምራቹን ዜጋ ለማፈራት እየተደረገ ላለው ጥረት እንቅፋት መሆኑን አስረድተዋል። ዶክተር ከይረዲን እንዳሉት በተለይም እንደ ሄሮይን፣ ኮኬየን፣ ሐሽሽ፣ ጫት፣ ትንባሆ፣ አልኮልና ሌሎችም ሱስ አስያዥ አደንዛዥ እፆችና መድኃኒቶች ከሚፈጥሩት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ባለፈ ለሞትና ለአዕምሮ በሽታም ይዳርጋሉ። በአገሪቱ የተጀመረውን የፀረ-ድህነት ትግል የሚያሰናክሉ በመሆኑም ሁሉም ባለድርሻ አካላትና መላው ሕብረተሰብ እየደረሰ ያለውን ጉዳት በመገንዘብ ችግሩን ለመከላከል በቅንጅት መስራት አንዳለባቸው አስገንዝበዋል። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ጋር በመቀናጀት ችግሩን ለመከላከል የሚያስችል የአምስት ዓመት ስትራቴጂ እቅድ ነድፎ ወደ ትግበራ ምዕራፍ ለመግባት ክልሎችን ያሳተፈ የንቅናቄ መድረክ እያካሄደ መሆኑን ገልጸዋል። በጋምቤላ የተካሄደውም የውይይት መድረክ የዚህ አካል መሆኑን ዶክትር ኸይረዲ አስታውቀዋል። የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኮንግ ጆክ በበኩላቸው "ጎጂ መጤ ልማዳዊ ድርጊቶችና አደንዛዥ እፆች የክልሉን ወጣቶች ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየዳረጋቸው ይገኛሉ" ብለዋል። እንደኃላፊው ገለጻ፣ ቢሮው ችግሩን ለመከላከል በሀገር አቀፍ ደረጃ የተነደፈውን የአምስት ዓመት እቅድ ከክልሉ ነባራዊ ሁኔታ በማጣጣም ለመተግበር ባለድርሻ አካላትን አካቶ መስራት ጀምሯል። "ወጣቶች ከአደንዛዥ እፆችና መጤ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲጠበቁ በወላጆች፣ በሕብረተሰቡና በክልሉ መንግስት የተሰራ ነገር የለም" ያሉት ደግሞ አቶ ኡቦንግ ኘየል የተባሉ የመድረኩ ተሳታፊ ናቸው። የወጣቱ ጉዳይ የማይመለከተው አካል ባለመኖሩ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ተቀናጅተው እንዲሰሩ ጠይቀዋል። "ወጣቱ ለአደንዛዥ እፆች ሱሰኝነት እንዲጋለጥ ከሚያደርጉት አንዱ የሥራ እድል እጦት በመሆኑ ሰርቶ መለወጥ የሚችልበት ሁኔታ ሊመቻችለት ይገባል" ያለው ደግሞ ወጣት ኡጁዶ ጋርቢ ነው። በመድረኩ ላይ ከተሳተፉ የአገር ሽማግሌች መካከል አቶ ኃይለማርያም ተክለማሪያም በሰጡት አስተያየት ''የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጋ መፍጠር የሚቻለው እኛ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በምንሰጠው ትምህርትና ምክር ነው'' ብለዋል። በመድረኩ በጋምቤላ ከተማ ችግሩን ለመከላከል የሚያስችል 22 አባላትና ባለድርሻ አካላት የተካተቱበት ግብር ኃይል ተቋቁሟል። በግብረ ኃይሉ የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች፣ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ፣ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማገሌዎች የተካተቱ ሲሆን ግብረኃይሉ የአምስት ዓመት እቅዱን በማስተግበር ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ የዘገበው ኢዜአ ነው።