"የመፈንቅለ መንግስት ሙከራና የግድያ ተግባር ያለንበት ዘመን የማይመጥን ነው" - የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
"የመፈንቅለ መንግስት ሙከራና የግድያ ተግባር ያለንበት ዘመን የማይመጥን ነው" - የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት
ሰኔ 18/2011 በአማራ ክልል የተደረገው "የመፈንቅለ መንግስት ሙከራና የግድያ ተግባር ያለንበት ዘመን የማይመጥን ነው" ሲል የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ። ምክር ቤቱ ለኢዜአ በላከው የፕሬስ መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በአማራ ክልል በተፈጸመው 'የመፈንቅለ መንግስት' ሙከራ ወቅት የክልሉን ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር አምባቸው መኮንን፣ የአደረጃጀት ዘርፍ አማካሪያቸውን አቶ እዘዝ ዋሴና የክልሉን ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ምግባሩ ከበደ እጅግ አሳዝኖታል፤ ድርጊቱንም አውግዟል። በአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ የመከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንን እና በጡረታ የተገለሉት ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ ላይ ተፈጸመው ግድያ ምክር ቤቱ በጽኑ እንደሚያወግዘው አስታውቋል። ሥልጣንን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ተወዳድሮ ማግኘት እንደሚቻል ያመለከተው መግለጫው፤ ሥልጣንን በሃይል ለመቀማት መሞከር ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውና ባለንበት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ኋላ ቀር አመለካከት እንደሆነ ገልጿል። ሥልጣንን በአቋራጭና በሃይል ለመያዝ የሚደረገው ጥረትም በጽኑ ምክር ቤቱ እንደሚያውግዘውና ተዋዶና ተከባብሮ የሚኖርባት ትልቅ አገርና ህዝብ የማይመጥን መሆኑን በመግለጫው ተመልክቷል። አገሪቷን ወደ ተሻለ አቅጣጫ ለመውሰድ ህዝባዊ ሃሳብ በፈለቀበት ዘመንና "ጥሩ አመራር አግኝተናል ብለን በተኩራራንበት ወቅት" ድርጊቱ መፈጸሙ ምክር ቤቱን እጅጉን እንዳሳዘነው አስታውቋል። በመሆኑም ከዚህ በኋላ መሰል ድርጊቶች እንዳይፈጸሙና ህዝቦች በተረጋጋ ሁኔታ ህይወታቸውን እንዲመሩ መንግስት የህግ የበላይነትን እንዲያስከብር ምክር ቤቱ ጠይቋል። መንግስት በድርጊቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላትን ህግ በሚፈቅደው አግባብና በፍጥነት አጣርቶ ጉዳዩን ለህዝብ እንዲያሳውቅ ምክር ቤቱ በመግለጫ አሳስቧል። ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን የተመኘው ምክር ቤቱ፤ "የተከሰተውን አጋጣሚ እንደ ትልቅ መንደርደሪያ ተጠቅመን ለአገራዊ ሰላምና አንድነት ልናውለው ይገባል" ብሏል።