"ጄኔራል ሰዓረ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ጀግና የአገር ልጅ ነበር" - ሌተናል ጄኔራል አበባው ታደሰ - ኢዜአ አማርኛ
"ጄኔራል ሰዓረ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ጀግና የአገር ልጅ ነበር" - ሌተናል ጄኔራል አበባው ታደሰ
ሰኔ 18/2011 "ጄኔራል ሰዓረ መኮንን በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ፍፁም ኢትዮጵያዊ ነበር" ሲሉ የቀድሞ የሥራ ባልደረባቸውና የቅርብ ወዳጃቸው ሌተናል ጄኔራል አበባው ታደሰ ገለፁ። የዛሬ ዓመት አካባቢ በጡረታ በክብርየተሰናበቱት ሌተናል ጄኔራል አበባው ይህንያሉት ባለፈው ቅዳሜ በጠባቂያቸው የተገደሉት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የጄኔራል ሰዓረ መኮንን አስከሬን በተደረገለት የሽኝት ስነ-ስርዓት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ነው። በዚሁ ጊዜ ሌተናል ጄኔራል አበባው እንዳሉት ጄኔራል ሰዓረ ከፍተኛ የዓላማ ጽናት ያላቸው፣ ከራሳቸው ይልቅ ምንጊዜም ለአገራቸውና ለህዝባቸው ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጡ ጀግና ኢትዮጵያዊ ነበሩ። በሙያቸውም በማንኛውም መንገድ የሚያጋጥም ጦርነትን ለመመከት የሚያስችል የአመራር ብቃትን የተላበሱ፣ አያሌ ጀግኖችንም ማፍራት የቻለ የጀግና ምሳሌ እንደነበሩም ነው እንባ እየተናነቃቸው የገለፁት። ከሁሉም በላይ ግን፤ በተለየ አገላለጽ በኢትዮጵያዊነታቸው የማይደራደሩ ፍጹም ኢትዮጵያዊ እንደነበሩ በመጠቆም በዚህ አቋማቸውም የተለያዩ ፈተናዎች ይገጥሟቸው እንደነበርም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ሌተናል ጄኔራል አበባው በጡረታ በክብር እስከተገለሉበት የዛሬ ዓመት አካባቢ ድረስ በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በከፍተኛ አመራርነት ያገለገሉ የጦር መሪ ነበሩ።