ለመንግስት ሰራተኞች የሚሰጡ ስልጠናዎቹ የላቀ አገልግሎት የሚያስገኙ ሊሆኑ እንደሚገባ ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
ለመንግስት ሰራተኞች የሚሰጡ ስልጠናዎቹ የላቀ አገልግሎት የሚያስገኙ ሊሆኑ እንደሚገባ ተገለፀ
ሰኔ 18/2011 የመንግስት ሰራተኛውን አቅም ለመገንባት የሚሰጡ ስልጠናዎች አገሪቷ የምትፈልገውን አገልግሎት ለማሻሻልና ለማጠናከር በሚያስችሉ ዘርፎችና ክህሎቶች ላይ ማተኮር እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩንቨርስቲ ገለፀ። ዩንቨርስቲው "የፐብሊክ ሴክተሩ ትራንስፎርሜሽን ያለበት ደረጃና የወደፊት አቅጣጫ"በሚል ርዕስ ዛሬ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል። በዚሁ ወቅት እንደተገለፀው በመላው ኢትዮጵያ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚጠጉ የመንግስት ሰራተኞች አሉ። የእነዚህን ሰራተኞች የእውቀትና ክህሎት አቅም ለማጠናከር በማሰብ በየዓመቱ ስልጠናዎችእንደሚሰጡም ተጠቁሟል። እስካሁንም በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ብቻ ከ150 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰራተኞች ከ78 በላይ በሚሆኑ ርዕስ ጉዳዮች ላይ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል። ዘንድሮም ከ8 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የመንግስት ሰራተኞች ስልጠና መዘጋጀቱን ዩኒቨርስቲው አስታውቋል። ሆኖም ሰራተኞቹ በተመደቡበት መስክ ውጤታማ በመሆን የሚጠበቅባቸውን መንግስታዊናህዝባዊ ኃላፊነት በብቃት መወጣት እንዲችሉ የሚሰጣቸው ስልጠና በጥናት ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት በስብሰባው ላይ ተመልክቷል። የዩንቨርስቲው የስልጠናና ማማከር ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ወጋሪ ነጋሪ በዚሁ ወቅት እንዳሉት እነዚህ የህዝብ አገልጋዮች ውጤታማ ተግባር መከወን እንዲችሉ የሚሰጣቸው ስልጠና አገሪቷ የምትፈልገውን አገልግሎት ለማሻሻልና ለማጠናከር በሚያስችሉ ዘርፎችና ክህሎቶች ላይ ማተኮር አለባቸው። ይህንን እውን ለማድረግ ወደፊት ሰልጣኞች የምስክር ወረቀት ከመውሰዳቸው በፊትና ስልጠና ከመግባታቸው በፊት የመለያ ፈተና የሚወስዱበት አሰራር ይዘረጋል ሲሉ ጠቁመዋል። የመንግስት ተቋማትን አስመልክቶ መነሻ ሃሳብ ያቀረቡት የመለስ ዜናዋ አመራር አካዳሚተመራማሪ ዶክተር እሸቱ አበበ እንደተናገሩት "ለዘርፉ የሚሰጠው ስልጠና መገምገምና ከአገሪቷ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ማጣጣም ያስፈልጋል።" በተለይም እስካሁን የተሰጡት ስልጠናዎች ያመጡት ለውጥ፣የአገልግሎት ቅልጥፍና፣ውጤታማነት፣ ተደራሽነት፣ስትራቴጂክ አካሄድ፣ቅንጅታዊ አሰራርና የስልጠና ወጪ በዝርዝርመታየት ይገባቸዋል ብለዋል። በተለይም ከተቋማት የሚመጡ ሰልጣኞች ስለ ስልጠናው ምንነት፣ ከስልጠናው የሚጠበቀው፣ ጥቅሙ፣ ፍላጎታቸውና የመሳሰሉት ላይ በቅድሚያ አቅጣጫና ማብራሪያ እንዲያገኙማድረግ ተገቢ ሲሉ አክለዋል። የውይይት መድረኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀ ሲሆን በቀጣይም በስፋት ለማካሄድ እቅድ መያዙ ተጠቅሷል።